::::::::::::::::::::::::::::::::::::::
በአምራች ኢንንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፍ ተሰማርተው የላቀ አፈጻጸም ላላቸው ኩባንያዎች እውቅና እና ሽልማት ተሰጠ።
ንጋት ኮርፖሬት የ2024 በጀት ዓመትን ዕቅድ ትግበራ በሥራ አመራር ቦርዱ ገምግሞ በማጠናቀቁ የቢዝነስ፣ ኢንቨስትመንት እና ማኅበራዊ ልማት ዋና ዋና ስኬቶች ይፋ አድርጓል።
የኮርፖሬቱ ቁልፍ ተልዕኮ ለአማራ ክልል እና ለሀገር ስትራቴጅያዊ ጠቀሜታ ባላቸውና አዋጭ በሆኑ የኢኮኖሚ መስኮች በመሠማራት የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ልማት ማምጣት ሲሆን የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ኩባንያዎች እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የ2024 እ.አ.አ በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም 1ኛ ደረጃ ሆኖ የተሸለመው በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኘው ዋልያ ቆርኪ ፋብሪካ ሲሆን፣ በ2ኛ ደረጃ አምባሰል የንግድ ሥራዎች እና በ3ኛ ደረጃ ግዮን ፕላስቲክና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ ኩባንያ ናቸው።

1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ተሸላሚዎች በኮርፖሬቱ በእድገት ደረጃ ተብለው በስትራቴጂ ትግበራ የከተለዩት ውስጥ ሲሆን፣ 3ኛ ደረጃ ተሸላሚው ግዮን ፕላስቲክ በመሠረታዊ ማሻሻያ ላይ የሚገኝና ዕድገት እያሳየ የመጣ አምራች ኢንዱስትሪ ነው።
የንጋት ኮርፖሬት የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ስዩም መኮንን እንደተናገሩት፤ ንጋት ኮርፖሬት በዕድገት ፍኖተ-ካርታው ያስቀመጣቸውን ግቦች ዕውን ለማድረግ ውጤታማ ቢዝነስ እና ኢንቨስትመንት እያካሄደ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚካሄዱ ስትራቴጂያዊ ትግበራዎች ተመጋጋቢ መሆን እንዳለባቸው ገልጸው ንጋት ኮርፖሬት ለዘላቂ ልማት መሠረት እየሆነ መጥቷል። በመሆኑም ኮርፖሬቱ ለሚያደርገው የልማት ሥራ ሁሉ የክልሉ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል ዘገባው የአማራ ኮሙኒኬሽን ነው።












