“ሶሪያ የዓለም ስጋት አትሆንም”-ኤችቲኤስ
፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ታህሳስ 10 2017| NBC ETHIOPIA- ሶሪያን የተቆጣጠረው የሃያት ታህሪር አል -ሻም መሪ አገሬ የዓለም ስጋት አይደለችም አሉ፡፡
ሶሪያን በመምራት ላይ ያሉት አህመድ አል -ሻራ ሶሪያ በጦርነት ደቃለች ያሉ ሲሆን ደማስቆ ለጎረቤቶቿም ሆነ ለምዕራቡ ዓለም ስጋት እንደማትሆን ይታወቅልን ብለዋል፡፡
ከቢቢሲ ጋር በደማስቆ ቆይታ ያደረጉት አል ሻራ በሶሪያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችም እንዲነሱ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡
ማዕቀቦች በሶሪያ ላይ የተጣሉት በአሮጌው አገዛዝ ነበር፤እናም ሊነሱ ይገባል በሚል ሃሳባቸውን አጋርተዋል ፡፡

የአገዛዙ ሰለባ የሆኑ ወገኖች በአሁኑ ሰዓትም በተመሳሳይ መንገድ ጫና ሊፈጠርባቸው አይገባም በሚልም አጽንዖት ሰተዋል፡፡
ሃያት ታህሪር አል -ሻም እና ሌሎች አጋሮቹ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የአሳድን አገዛዝ አፍርሷል፡፡
በቅጽል ስማቸው አቡ መሀመድ አል -ጁላኒ በሚል የሚጠሩት የHTS ሀይሎች መሪ ሶሪያን ለማረጋጋት እና ህዝቧን ለመታደግ ከሁሉም ሀይሎች ጋር እንስራለን ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ቡድናችን ከአሸባሪነት ዝርዝር መውጣት አለበት በሚል ሀሳባቸውን አጠናክረዋል፡፡
ሃያት ታህሪር አል-ሻም በመንግስታቱ ድርጅት፣በአውሮፓ ኅብረት፣በአሜሪካና በብሪታንያ አሸባሪ ተብሎ መፈረጁ አይዘነጋም፡፡
በ-ቢኒያም ካሴ












