፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ታህሳስ 10 2017| NBC ETHIOPIA-የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በሀገሪቱ ስንዴ አብቃይ አካባቢዎች እየተከናወነ ያለው የስንዴ ልማት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ መንግስት ስንዴን ወደ ውጭ መላክ የጀመረውን ሥራ የሚያጠናክር ነው መሆኑን ገለጹ።
በባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የተመራ ቡድን በአሪ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ ወሰት ቀበሌ በ77 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የለማ የስንዴ ማሳን ጎብኝቷል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ መንግስት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ሀገር የሚያስገባቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካት የሚያስችል ኢኒሼቲቭ ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
በሀገሪቱ ስንዴ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች እየተከናወነ ያለው የስንዴ ልማት መንግስት የሀገር ውስጥ ፍጆታን በመሸፈን ወደ ውጭ መላክ የተጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የስንዴ ልማት ሥራው የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እንደሚያስችል ገልፀው የደቡብ አሪ ወረዳ ተሞክሮ በሌሎች አካባቢዎችም መስፋት እንዳለበት ተናግረዋል።
የአሪ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታፈሰ ተስፋዬ በበኩላቸው ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የግብርና ምርቶችን በብዛትና በጥራት በማምረት ምርታማነትን በእጥፍ ለማሳደግ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን መጠቀም ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
በወሰት ቀበሌ በኩታ ገጠም በክላስተር እየለማ ባለው 77 ሄክታር ማሳ ላይ ከ100 በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ አቶ ታፈሰ ጠቁመዋል።
ከአርሶ አደሮቹ መካከል አቶ ፈራጅ ዝንጎ እንደተናገሩት፥ በአካባቢው የስንዴ ልማት የቆየ ቢሆንም የነበረው ባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ አርሶ አደሩ የልፋቱን ያህል ውጤት እንዳያገኝ ሲያደርገው መቆየቱን ገልጸዋል።
የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በኩታ ገጠም ስንዴ ማልማት ከጀመሩ ወዲህ የተሻለ ውጤት እያገኙ መሆኑንም አክለዋል።
የኩታ ገጠም እርሻው አረምና ተባይ በጋራ ለመከላከል እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ የገለፁት ሌላው አርሶ አደር ደግሞ ማቴዎስ መልቲ ናቸው።
ለእርሻ ሥራው ውጤታማነት መንግስት ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ በወቅቱ ከማቅረብ ጀምሮ ስለ ዘመናዊ እርሻ ግንዛቤ በማስጨበጥ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች ስንዴን ጨምሮ ሌሎች የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን በስፋት እያመረቱ እንደሆነ ገልፀው፥ ምርቱን ወደ ገበያ ለማቅረብ ያለባቸው የመንገድ ችግር እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት በአካባቢው ያለውን የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር ለመፍታት በዞኑ፣ በክልሉና በፌዴራል አቅም የሚከናወኑ ሥራዎች እንዳሉ ጠቁመው፤ በቀጣይ በዚሁ መሰረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
አርሶ አደሮቹ በሜካናይዜሽን እርሻ ሥራ ላይ በመሳተፍ በስፋት ሰብሎችን የሚያመርቱበትና ለገበያ የሚያቀርቡበት ሁኔታም ይመቻቻል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።












