የሬጌው ንጉስ ሲል ዓለም በአንድ ድምጽ ይስማማበታል በሙዚቃው የሰላምን ዋጋ አስረድቶ አቀንቅኖ የተጣሉትን አስታርቋል፡፡
ጭቆናን በሚተቹ እና አንድነትን በሚሰብኩ ዘፈኖቹ ዝናና ተወዳጅነትንም አትርፏል፡፡ ታላቁ የሬጌ አቀንቃኝ፣ ሙዚቀኛ እና አቀናባሪ ሮበርት ኔስታ ማርሊ ወይም ቦብ ማርሌይ፡፡
የሬጌ ሙዚቃን በመጫወትና ለሕዝቡ እንዲደርስ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው ቦብ የሬጌ ሙዚቃ ፈር ቀዳጅና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ እንዲሆን ካደረጉት መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል ፡፡
ከዚህ ዓለም በለጋ እድሜው የተለየው ቦብ እ.ኤ.አ በ1980 በትላንትናው እለት ነበር የመጨረሻ ኮንሰርቱን ለአድናቂዎቹ ያደረሰው፡፡ በወቅቱ በአውሮፓ የተዘጋጀ ትልቅ ኮንሰርት ነበር ፡፡

ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰብ የተወለደው ቦብ ህይወቱን ለማሸነፍ መጣር የጀመረው ገና በልጅነቱ ነበር ፡፡ የሙዚቃ ሕይወቱንም ሀ ብሎ የጀመረው በ1960ዎቹ መጨረሻ አካባቢ እንደሆነ ታሪኩ ያወሳል ፡፡ Judge Not የተሰኘው ዘፈኑ የመጀመሪያ ስራው ነው ፡፡
ቦብ በ17 አመቱ ፒተር ቶሽ እና በኒ ዌይለር ከተባሉ ጓደኞቹ ጋር በመሆን ዘ ዌይለርስ የተባለ ቡድን በመመስረት ዘፈኖችን ለአድማጭ ማድረሱን ቀጠለ ፡፡ ነገር ግን ብዙም እንዳልተደመጠ ይነገራል ፡፡

በዚህ ተስፋ ያልቆረጠው ቦብ ማርሌይ በ1975 የለቀቀው No Woman, No Cry የተሰኘ ስራው ከጃማይካ ውጪ በከፍተኛ ደረጃ በመደመጥ ቻለ ፡፡ በመቀጠልም Rasta man Vibration የተሰኘ ሌላ ስራን በመልቀቅ የቢልቦርድ ሰንጠረዥን በመያዝ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን ማግኘት ችሏል ፡፡
13 የስቲዲዮ አልበሞች ፣ ስድስት Live አልበሞች እና 133 ነጠላ ዜማዎች እና የሌሎች ስራዎች ባለቤት ነው ፡፡ በመላው ዓለም እየተዛወረም በርካታ አድናቂዎቹ በተገኙበት የኮንሰርት ስራዎቹን አቅርቧል ፡፡
በሚሰራቸው ተሰምተው የማይጠገቡ ስራዎቹ ዝናው እየናኘ የመጣው ቦብ 1976 በትውልድ ሀገሩ ጃማይካ የተቀጣጠለውን የፖለቲካ ግጭት ለማብረድ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተዘጋጀ Smile Jamaica በተሰኘ ኮንሰርት ላይ ለመዝፈን ሁለት ቀን ሲቀረው በተቃዋሚዎች እሱ ፣ ባለቤቱ ሪታ ማርሌ እና ማናጀሩ ላይ ጥቃት አድረሰውባቸው ነበር ፡፡

ይህም ለቦብ ከሀገሩ መሰደድ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል ፡፡ ወደ ለንደን በማቅናትም ታይም መጽሄት የ20ኛው ክፍለ ዘመን ምርጡ አልበም ያለውን Exodus የተሰኘ ስራውን ለአድናቂዎቹ አድርሷል፡፡
ከሙዚቃ በተጨማሪ የስፖርት እንቅስቃሴ እንደሚያዝናናው የሚናገረው ቦብ እግር ኳስ ሲጫወት እግሩ ላይ የደረሰበት ጉዳት ወደ ካንሰርነት ተቀይሮም ነበር፡፡
በወቅቱም አውራ ጣቱ እንዲቆረጥ ሀኪሞች ቢመክሩትም የሚከተለው ሀይማኖት እና የራስ ተፈሪያን ሥርዓቱ ባለመፍቀዱ የሀኪሞቹን ሀሳብ ሳይቀበል ቀረ ፡፡
ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ህመሙ እየተባበሰ ቢመጣም በ1980 Uprising የተሰኘ አልበሙን በማስመልከት በተለያዩ ሀገራት እየተዛወረ ስራዎቹን ማቅረብ ጀመረ ፡፡ በሲዊዘርላድ የጀመረው ኮንሰርቱ እ.ኤ.አ 1980 በትላንትናው እለት በPittsburgh ፍጻሜውን አገኘ ፡፡ ከዚህ ኮንሰርት በኋላ ቦብ የቆየው ለወራት ብቻ ነበር ፡፡
በተለያዩ ሀገራት ህክምናውን ሲከታተል የቆየው ቦብ በ1981 በ36 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየ ፡፡

ህይወቱ ካለፈ በኋላ የተለቀቀው Legend የተሰኘ ስራው በመላው አለም ከ12 በላይ ቅጂዎቸ በመሸጣቸው የምንግዜውም ምርጥ የሬጌ አልበም መሆን ችሏል፡፡
ፎርብስ መጽሄት በህይወት ሳይኖሩ ከፍተኛ ገቢ ከሚያገኙ ሰዎች መካከል አካቶታል ፡፡
ቦብ ማርሌይ በጥቂት እድሜው የሰራቸው በርካታ ሙዚቃዎች አብዛኞቹ በጥቁር መብት እና በአፍሪካ ፖለቲካ ላይ ያጠነጠኑ ናቸው ፡፡

ቦብ ማርሌይ ስለአንድነት፣ ስለሰዎች እኩልነት፣ ስለዓለም ሰላም በማቀንቀን መልካም አስተሳሰብን የሚዘክሩ ጠንካራ ሐሳቦችን በሬጌ የሙዚቃ ሥልት አዋዝቶ ለሕዝቡ በማቅረብ ትልቅ ሥራዎችን ሠርተው ካለፉ ዘፋኞች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው ፡፡
በ70ዎቹ እና በ80ዎቹ ብቅ ብሎ አሁንም ድረስ በሰዎች ልብ ውስጥ ስላለው ዘመን አይሽሬው ቦብ ማርሌይ የመጨረሻ ኮንሰርቱን ያቀረበበትን ቀን እንዲህ አስታወስናችሁ፡፡












