የሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በላልይበላ ከተማ አስተዳደር ተገኝተው የተጠናቀቁና በቅርብ ወራቶች ተጠናቀው ወደ ስራ የሚገቡ ፕሮጀክቶችን የመስክ ላይ ጉብኝት አደርገዋል።
በመስክ ጉብኝቱ አቶ ታምራት ንጋቱ የሰሜን ወሎዞን ምክትል አስተዳዳሪና የንግድናገበያ ልማት መምሪያ ሀላፊ፣ የሰሜን ወሎ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ፅ/ቤት አደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ ክብርት አታላ አያሌው፣ የሰሜን ወሎ ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ሀላፊ አቶ ሞላ ደሱ፣ የሰሜን ወሎ ዞን ሰላምና ደህንነት ሀላፊ ሻንበል ቢሰጥ እንዲሁም የላልይበላ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ጉብኝት አድርገዋል፡፡
ቡድኑ የከተማ አስተዳደሩን የቢሮ ግንባታ፣ ናአኩቶልአብ እና ለውዝ /ቻይና ካምፕ /በፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ተሰርተው የተጠናቀቁ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን፣ በፌደራል መልሶ ማቋቋም የተገነባውን ሲመኖ አንደኛና መካከለኛ ት/ቤት እንዲሁም የላልይበላን የውሀ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከሽምሽሀ የሚመጣውን ውሀ መግፊያ ሶላር እና ከአውሮፓ የመጡትን መገጣጠሚያ መሳሪያወችን እንዲሁም ሲመኖ እና ቅዱስ ናአኩቶልአብ በኢንቨስትመንት ቦታ ተስጥቷቸው እየተሰሩ ያሉ 2 የነዳጅ ማደያወችን እንዲሁም ናአኩቶልአብ ቀበሌ የሚገኘውን የጠጠር ማምረቻ ክሬቸር ጎብኝተዋል፡፡
የጉብኝቱ ዓላማ በከተማዋ እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች፣ የተሻሉ አፈፃፀም ላይ ያሉትን ለማበረታታት ክፍተት ያለባቸውን ለማረም ያግዝ ዘንድ ከሁሉም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የመስክ ምልከታ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አማራ ኮሙኒኬሽን ዘገባ ያመለክታል፡፡












