፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ነሐሴ 25 2016| NBC ETHIOPIA-በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ከፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ጋር ጭምር በመቀናጀት በተደራጀ መንገድ እየሠራ እንደሚገኝ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው ገልጸዋል።
ኃላፊው እንዳሉት የጸጥታ መዋቅሩ ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ ተግባራትን እንዲያከናውን የማደራጀት፣ ቅንጅታዊ አሠራሩን የማጠናከር እና የአቅም ግንባታ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ሕግ የማስከበር ተግባር እና ኃላፊነት የጸጥታ መዋቅሩ ብቻ አለመሆኑን ያነሱት ኃላፊው ማኅበረሰቡም ለጸጥታ መዋቅሩ በሞራል በመደገፍ ወንጀልን መከላከል፣ በጸጥታ መዋቅሩ የሚታዩ የሥነ ምግባር ችግሮች ካጋጠሙ ደግሞ የመታገል ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል።
በየቦታው የሚሠሩ ሕገ ወጥ ተግባራትን ዘላቂነት ባለው መንገድ ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል ሲል የዘገበዉ አሚኮ ነዉ።












