፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ነሐሴ 17 2016| NBC ETHIOPIA- የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአይሲቲ ፓርክ ተገኝተው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ላይ አሻራቸውን አኑረዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ አረንጓዴ አሻራን ማኖር ለዛሬ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለነገውም ትውልድ ትልቅ ትሩፋት መሆኑን ገለጹ።
ከንቲባዋ በመዲናዋ በ250 ሄክታር መሬት ላይ የ6 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ እየተከናወነ ነው ያሉት ህዝቡም በነቂስ ወጥቶ እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማዋ ባለፉት አምስት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች 86 በመቶ መጽደቃቸውን ጠቅሰው፣ በዚህ ዓመት የአረንጓዴ ሽፋኑ እያደገ መምጣቱን ነው ያነሱት።
የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋን ከአምስት ዓመታት በፊት 2 ነጥብ 8 በመቶ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ጊዜ የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋን 20 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።
የአረንጓዴ ሽፋናችንን መጨመር ለወደፊት የሀገራችን ብልፅግና መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው ብለዋል።አረንጓዴ አሻራን ማኖር ለዛሬ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለነገውም ትውልድ ትልቅ ትሩፋት መሆኑን ገልጸዋል። ችግኝ ለመትከል የታየው መነሳሳት በእንክብካቤ ላይም ሊደገም እንደሚገባ ነው ጥሪ ያቀረቡት።
በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር አዋቂዎች ከ20 በላይ፤ ታዳጊዎች ደግሞ ከ10 በላይ ችግኞችን ይተክላሉ ተብሎ ይጠበቃል።












