፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሐምሌ 26 2016| NBC ETHIOPIA- ኢራቅ ከአሜሪካ መራሹ 42 ሃገራት ጥምረት ጋር የገባችበት የባህረ ሰላጤው ጦርነት መንስኤ ከዛሬ 34 ዓመታት በፊት በጎርጎሮሳውያኑ ነሀሴ 2 1990 ተከሰተ፡፡ የኢራቅ ኩዌት ወረራ፡፡
በወቅቱ ኢራቅ ኩዌት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በእንግሊዝ አጉል ሀገር ነሽ ተብላ የልብ ልብ ተሰምቷት እንጂ የግዛቴ አካል ናት የሚል አቋምን ታራምድ ነበር፡፡
ኢራቅ በጎርጎሮሳውያኑ ከመስከረም 1980 እስከ ነሐሴ 1988 ከኢራን ጋር ከባድ ጦርነት ውስጥ ገብታ ነበር፡፡ የመጀመሪያው የባሕረ ሰላጤ ጦርነት በመባል ይታወቃል፡፡ ጦርነቱ ሲያበቃ ለጦርነቱ ማስኬጃ ከኩዌት የተበደረችውን 14 ቢሊዮን ዶላር እዳ የምትመልስበት አቋም ላይ አልነበረችም ኢራቅ፡፡ በመሆኑም እዳዋን ትሰርዝላት ዘንድ ኩዌትን ብትማጸንም ይሁኝታን አላገኘችም፡፡ ይህ የኩዌት እንቢተኝነት ኢራቅን ቂም እንድትይዝ አደረጋት፡፡
ለነዳጅ ቁፋሮ ኢራቃውያን የኩዌትን ድንበር መሻገራቸው ቁርሾውን እያከፋው ሄደ፡፡ ታዲያ አምስተኛው የኢራቅ ፕሬዚዳንት የሳዳም ሁሴን አስተዳደር ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ በግልጽ መዛት ጀመረ፡፡
የወረራው ጭምጭምታ የደረሳቸው የኩዌት ኢሚር ሼክ ሳበር አል-አህመድ አል-ሳባህ፣ ቤተሰቦቻቸው እና ሌሎች ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ከወረራው ጥቂት ሰዓታትን ቀደም ብሎ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ሸሹ፡፡ በመካለኛው ምስራቅ መገኛዋን ያደረገችው ኢራቅ በነዳጅ የበለጸገችዋን ጎረቤቷን ኩዌት ከባ ነሃሴ 2፣ 1990 ወረረች፡፡

ከዓለም የነዳጅ ክምችት የ20 በመቶው መገኛዋን ኩዌት በቁጥጥሯ ስር ለማዋል እና መንግሥት ለማቋቋም ከሰዓታት በላይ አልፈጀባትም፡፡ በሁለት ቀናት ውስጥ ሙሉ ኩዌትን ተቆጣጠረች፣ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚገኘውን ከፍተኛ መጠን ያለው የባሕር ዳርቻም በስሯ አደረገች፡፡ ሉኣላዊቷን ሀገር ኩዌት በስተሰሜን እና በስተደቡብ ለሁለት ከፈለቻት፡፡
የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የእዛኑ ቀን ጊዜ ሳያጠፋ በአንድ ድምጽ ወረራውን አውግዞ ኢራቅ ከኩዌት ምድር በአፋጣኝ እንድትለቅ አዘዘ፡፡ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እና ማዕቀብ መጣል የሰርክ ስራው ሆነ፡፡
ኢራቅ ትዕዛዙን አሻፈረኝ በማለቷ ድርጅቱ በአራተኛው ቀን የትኛውም የዓለም ሀገር ከኢራቅ ጋር የንግድ ልውውጥ እንዳይኖረው “የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በውሳኔ ሀሳብ 678 ዓለም ዓቀፍ እገዳ ባግዳድ ላይ ጣለ፡፡ እገዳው ኢራቅ ያወደመቻትን ኩዌት መልሳ እንድታቋቁም ግዴታ የሚጥል ሲሆን እስከ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 22፣ 2003 ቆይቷል፡፡
ውሳኔው ኢራቅን የሚገታት አለመሆኑን ሲገነዘብ ድርጅቱ የአባል ሀገራቱን ጦር ህብረት ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸር እና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ወታደሮቻቸውን ከነሙሉ ትጥቅ በሳውዲ አረቢያ አሰፈሩ፡፡ ሌሎች ሃገራትም ጊዜ ሳያጠፉ ጥምረቱን ተቀላቀሉ፡፡
ጥምረቱ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁ ወታደራዊ ጥምረት ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል ከጥምረቱ አብዛኛውን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን ሳዑዲ ዓረቢያ፣ እንግሊዝ እና ግብጽም ትልቅ ድርሻ ነበራቸው፡፡ ጥምረቱ ኢራቅን ለመዋጋት 60 ቢልዮን ዶላር ወጪ ያደረገ ሲሆን ከእዚህ ውስጥ 32 ቢልዮን ዶላሩን የሸፈኑት ሳውዲ አረቢያ እና በስደት ላይ የነበረው የኩዌት መንግሥት ነበር፡፡
በስተመጨረሻም ጥምረቱ እስከ ጥር 15 ቀን 1991 የሳዳም ሁሴን ጦር ከኩዌት ምድር ጠቅልሎ እንዲወጣ የመጨረሻ እድል መስጠቱን አስታወቀ፡፡ ማሳሰቢያው ምላሽ ባለማግኘቱ በጥር 17 የህብረቱ ተዋጊ ጀቶች በኢራቅ ኢላማዎች ላይ ከፍተኛ ድብደባ ማድረግ ጀመሩ።
ጥምር ጦሩ የኢራቅን ጦር ወታደራዊ ኢላማዎች አወደመ፣ ኢራቅ በምላሹ በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሶቪየት ህብረት በተመረተው አደገኛ የባሊስቲክ ሚሳኤል ጥምረቱ ላይ ጥቃት ሰነዘረች፡፡


ይሁን እንጂ እድል አብሯት ሊቆይ አልቻለም፡፡ የሳዳም ሁሴኗ ኢራቅ ድል እየተደረገች ወደኋላ ማፈግፈግ ጀመረች፡፡ በጦርነቱ እስከ 50 ሺህ የሚደርሱ ወታደሮቿ ሲገደሉባት 75 ሺህ ገደማዎቹ ቆስለውባታል፣ 175 ሺህ ተማርከውባታል፣ ከ3 ሺህ በላይ የጦር ታንኮቿ እና ከ2 ሺህ በላይ ሌሎች የውጊያ ተሽከርካሪዎች ወድመውባታል፡፡ በአጸፋው በጥምረቱ ላይ ያደረሰችው ጉዳት አነስተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በአየርና በምድር ጥቃት ከታጀበ ከሰባት ወራት ቆይታ በኋላ እድሜ ለአጋሮቿ ኩዌት ነጻነቷን ተቀዳጀች፡፡ የኩዌት ምድር ሰላም ሲሰፍንበት ጥምረቱ ወደኢራቅ ምድር ዘልቆ ዳግም መሰል ነገር እንዳትሞክሪ የሚመስል ወታደራዊ እርምጃ ወሰደ፡፡ 2 ሺህ ወታደሮች በ400 ገደማ ሄሊኮፕተሮች ወደ ኢራቅ ተጉዘው የኢራቅን ምድር አስጨነቁት፡፡
ለመሸሽ የሚሞክረውን የሳፋም ሁሴን ጦር ማርከው መጠነ ሰፊ ጥቃት ሰነዘሩ፡፡ በስተመጨረሻም በየካቲት 28 በተኩስ አቁም ስምምነት መቋጫውን አገኘ፡፡
ይህን ኢራቅ ከ42 ሃገራት ጥምረት ጋር የገባችበት የባህረ ሰላጤው ጦርነት መንስኤ የሆነው የኢራቅ ኩዌት ወረራ የተከሰተበትን የዛሬውን ቀን ተንተርሰን ጥቂት አልናችሁ፡፡
በ-መቅደስ ደምስ












