፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሐምሌ 26 2016| NBC ETHIOPIA- የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ አፈጉ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በ2016 በጀት ዓመት በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ዕቅዱን በተገቢው መንገድ መፈጸም አልተቻለም ነው ያሉት።
አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፍነው የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ በማረጋጋት፣ ለልማት እና መልካም አስተዳደር ምቹ በማድረግ ነው ብለዋል።
ከጸጥታ ሥራው ጎን ለጎን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች መሥራታቸውንም አመላክተዋል። በተለይም አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች በርካታ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች መሠራታቸውን ነው የተናገሩት።
የ2017 በጀት ዓመት ያለፈው ዓመት እና ከዚያ በፊት በነበሩ ጊዜያት ያልተፈጸሙ ሥራዎች ጭምር የሚሠሩበት ነው ብለዋል። የ2017 በጀት ዓመት ያለፉት የስትራቴጂክ ዕቅድ ዓመታት ማጠናቀቂያ መሆኑንም አንስተዋል።
በበጀት ዓመቱ ከታቀዱ ሥራዎች ባለፈ ሌሎች ሥራዎች የሚሠሩበት እንደኾነም ተናግረዋል። የ2017 በጀት ዓመት ከ2018 እስከ 2022 ዓ.ም ለሚዘልቀው የአምስት ዓመታት የስትራቴጂክ ዕቅድ ለመፈጸም የሚያስችሉ ዝግጅቶች የሚደረጉበት መሆኑንም ገልጸዋል።
የ2017 በጀት ዓመት ያለፈው ችግር ጥላውን እንዳያጠላበት የሚደረግበት ዓመት ነው ብለዋል። በመንግሥት እና በፓርቲ ቅንጅት በመፍጠር የተሻለ ሥራ ለመፈጸም ግዴታ የሚገባበት ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ትልቅ ፋይዳ ያለው መኾኑንም አመላክተዋል። ጊዜን በመሻማት የተሻለ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ዕቅዳቸውን በምክር ቤት አጽድቀው ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅታቸውን መጨረሳቸውንም ተናግረዋል።
የክልሉን ርዕይ የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል። ፍኖተ ካርታው ችግሮችን እና ጥንካሬዎችን በመለየት መልካም ሥራዎችን ለመሥራት እንደሚያስችልም አመላክተዋል።
የታቀደው ዕቅድ የቁጭት ዕቅድ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ከችግር በመውጣት ስኬታማ ደረጃ ላይ ለመድረስ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። በከፋ ችግር ውስጥ ቆይተው በሠሩት ሥራ ስኬታማ ከሆኑ ሀገራት ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባም አመላክተዋል።
በበጀት ዓመቱ በእያንዳንዱ ቦታ በመግባባት ውጤታማነት የሚረጋገጥበት ነው ብለዋል። የክልሉን የጸጥታ ችግር በማስተካከል እና የውስጥ አቅምን በመጠቀም ሕዝብን ከችግር ለማላቀቅ መስራት ይገባል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCEthiopiaSC
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












