፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሐምሌ 18 2016| NBC ETHIOPIA-አለም በየቀኑ ከአራቱም አቅጣጫ አስገራሚ ክስተቶችን ታስተናግዳለች ፡፡ እኛም ከሰሞነኛ አስገራሚ እና አነጋጋሪ ጉዳዮች ጥቂቶቹን እንካቹ ልንላቹ ወደድን ፡፡
የመጀመሪያው አስገራሚ ጉዳያችን በ98 አመታቸው ዶክቴሬት ዲግሪ የተሰጣቸው አዛውንት ናቸው ፡፡ ሮስሜሪ ፎውለር ይባላሉ ከ75 ዓመታት በፊት ወደ ትዳር መግባታቸውን ተከትሎ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሳይቀበሉ ትምህርታቸውን ስለማቋረጣቸው ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ከበርካታ አመታት በኃላ የ22 አመት ወጣት ሆነው የተሰናበቱት የቀድሞ ዩኒቨርሲቲያቸው የ98 አመት አዛውንት ሆነው የክቡር ዶክትሬት ማበርከቱ በበርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

1948 በኢንግላንድ በሚገኘው ብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ተማሪ በነበሩበት ወቅት ባደረጉት ምርምር ካኦን የተሰኘ ቅንጣትን አግኝተው እንደነበርም ተገልጿል፡፡ ይህን ከግምት በማስገባት ነው በማምሻ እድሜያቸው የክብር ዶክተሬት ካባን የተጎናጸፉት፡፡
ሌላኛው አስገራሚ ጉዳያችን ከወደ ታይላድ የተሰማ ነው ፡፡ በሀገረ ታይላንድ እና ላኦስ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ኮይ ፕላ የተሰኘ ከጥሬ አሳ የሚዘጋጅ ተወዳጅ ባህላዊ ምግብ አላቸው፡፡

ታዲያ የሀገሬው ሰዎች ተወዳጅ ምግብ በየአመቱ በታይላድ ብቻ 20ሺ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑ ነው ኦዲቲ ሴንተራል ያስነበበው፡፡
ምግቡ በዋነኛነት የሚዘጋጀው በተፈጨ ጥሬ አሳ፣የሎሚ ጭማቂ፣ ቅጠላቅጠሎች እና ቅመሞችን በመጠቀም ሲሆን ዋነኛ ችግሩም አሳው ስለመሆኑ በተደረጉ ጥናቶች የተለየው፡፡እናም በአሳው ላይ የሚገኙ ጥገኛ ተዋሲያን አስከፊ የካንሰር በሽታን እንደሚያስከትሉ ስለመሆናቸው እና 20 ሺህ ሰዎችን በየዓመቱ እየገደለ ስለመሆኑ የተነገረው ፡፡
አስገራሚው የሎተሪ እጣ አሸናፊ በሚል መነጋገሪያ ሆኗል ፡፡ ህልሙ አንድ ሚሊዮን ዶላር እንዲያሸንፍ ያደረገው ግለሰብ ፡፡
የፕሊማውዝ ነዋሪው ሃዋርድ ኬንድል ጁኒየር በህልሙ በ10 ዶላር የሚሸጥ ሎተሪን ገዝቶ አራት ሚሊዮን ዶላር ሲደርሰው እንዳየ ይናገራል ፡፡

ነገር ግን ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነሳ እንደማንኛውም ሰው ህልም ነው ብሎ ማለፍ ያልፈለገው ሃዋርድ ይልቁንም ህልሙን እውን ለማድረግ አቅራቢው ወደሚገኝ ሎተሪ መሸጫ በመሄድ አንድ የሎተሪ ትኬትን ይገዛል ፡፡ ትኬቱም የአንድ ሚሊዮን ዶላር አሸናፊ ሊያደርገው ችሏል፡፡
በ-የአብስራ ብርሀኑ












