፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሐምሌ 18 2016| NBC ETHIOPIA-አሁን ላይ ተሽከርካሪዎች ከሚሰጡት ግልጋሎትና ካላቸው ፋይዳ አንጻር ተፈላጊነታቸው በእጅጉ እያየለ መጥቷል፡፡
መኪኖች ቀድሞ በነበረው ጊዜ ግልጋሎታቸው ሰዎችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ከማሸጋገር እምብዛም ያልበለጠ ነበር፡፡
ሆኖም ከጊዜ ወደ ጊዜ በርካታ የመኪና አምራች ድርጅቶች የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የመኪኖችን ግልጋሎት አይነትን አስፍተዋል፡፡እነዚህ ተሸከርካሪዎች ቅንጡ ቤቶችን ጨምረው የያዙና የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ችለዋል፡፡
በብዙዎች ተፈላጊ እየሆኑ የመጡ አምስት ተሸከርካሪዎችን እነሆ፡፡
👉 የደምበል ሞተር ሆም

ደምበል የተሰኘው ግዙፍ ተሽከርካሪ በገጽታው እንደሚታየው ተሸከርካሪ ብቻ አይደለም፡፡በውስጡ እጅግ የተዋቡና ቅንጡ መኖሪያ ቤትን ጨምሮ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ገጽታው በእጅጉ የተዋበ ነው፡፡
ተሸከርካሪው 12 ሜትር ርዝመትና 2.5 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን አነስ ያለ ጋራዥና ኩሽና በተጨማሪም አንድ የመኝታ ክፍል የያዘ ነው፡፡አራት ሰዎችን በፍፁም ምቾት ሊመግብ የሚችል መመገቢያ ስፍራን ያካተተ ነው፡፡
ኩሽናው እና አስፈላጊ መገልገያዎችን ጨምሮ ማቀዝቀዣ ፍሪጅ የያዘ ነው፡፡ደምበል የተሰኘው ተሽከርካሪ ቤት በ1 ነጥብ 25 ሚሊዮን ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡
👉ፐርፎርማንስ ኤስ ሞተር ሆም

በጀርመን የቅንጦት የሞተር ሆም አምራች ድርጅት ይፋ የተደረገው ፐርፎርማንስ ኤስ የተሰኘው ተንቀሳቃሽ መኖሪያ ቤት ለገበያ የቀረበው በፈረንጆቹ 2021 ነበር፡፡
መኖሪያ ቤትን ያካተተው ተሽከርካሪ ተንቀሳቃሽ ጋራዥ ከመያዙ በላይ መኝታ ክፍል እና ሻወርን አካቶ ይዟል፡፡ ፐርፎርማንስ ኤስ ኩሽና እቃ ማጠቢያና ማቀዝቀዣም ያለው ተሸከርካሪ ነው፡፡
በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ውድ የሞተር ቤቶች አንዱ ሲሆን ዋጋው እስከ 7 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር ይደርሳል ተብሏል፡፡
👉stx ሞተር ሆም

ይህ ተሽከርካሪ በላቁ ቴክኖሎጂዎችና አዳዲስ የደህንነት ስርዓቶችን ጨምሮ የተለያዩ የአሽከርካሪዎች እገዛ ስርዓቶችን አጠቃሎ የያዘ ነው፡፡
የተሸከርካሪው ሞዴል ሙሉ ለሙሉ የተሟላ ኩሽና ያለው ሰፊ እና ምቹ የመኖሪያ ቦታን ያካተተ ነው፡፡ምቹ መታጠቢያ ቤትና ያማረ መኝታ ቤት በዚህ ተሽከርካሪ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡
ግዙፍ ምቹ የመኖሪያ ቦታ የተሟላ ኩሽና፣ ደረጃውን የጠበቀ መታጠቢያ ቤትና ሰፊ የመኝታ ክፍሎች የተሸከርካሪው አካል ናቸው። ይህ ሞዴል ስኩተሮችን፣ብስክሌቶችንና እንዲሁም ተጨማሪ መጫወቻዎችን ማከማቸት የሚችል ነው፡፡
👉ኤሊያም ሜን ፓላዞ ሞተር ሆም

ኤሊያም ሜን ፓላዞ ሞተር ሆም በአውስትራሊያ ኩባንያ የተሰራ የቅንጦት ሞተር ቤት ወይም የመዝናኛ ተሽከርካሪ ነው።
ኤሊየም ሜን ፓላዞ በቅንጡነቱ ይዘቱ የብዙዎችን ቀልብ መሳብ ችሏል፡፡ፓላዞ ባለ ከፍተኛ የስፖርት መኪና ወይም የቅንጦት ጀልባ የሚመስል ኤሮዳይናሚክ ዲዛይን ገጽታ አለው፡፡ ከ12 እስከ 20 ሜትሮች ባለው ርቀት በተለያየ ርዝመት ማግኘት ይቻላል፡፡
በውስጡ ሰፊ የመኖሪያ ክፍል እና የመዝናኛ ቦታዎች ያካተተ ሲሆን ማንኛውንም የቤት ውስጥ አገልግሎት በመኪናው ላይ ማግኘት እንዲቻል ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡
ይህ ቅንጡ ተሽከርካሪ እስከ አንድ ሚሊየን ዶላር እንደሚሸጥ ዋጋ ወጥቶለታል፡፡
👉ፉሪዩን ኤልሲዩም ሞተር ሆም

ኤሊሲየም ከቅንጦት የመዝናኛ ተሽከርካሪዎች ውስጥ የሚካተት ነው፡፡
ከሌሎቹ በተለየ መልኩ ልዩ ትኩረትን እንዲስብ ያደረገው ጣሪያው ኤሊኮፍተርን ማሳረፍ የሚችል መሆኑ ነው፡፡በተሸከርካሪው ውስጥ 45 ጫማ ርዝመት ያለው ዘመናዊ ኩሽና ምቹ መቀመጫና የመመገቢያ ቦታን ያካተተ ሆኖ ተሰርቷል።
አረፍ ለማለት የሚያስችሉ ቅንጡ ሶፋዎችንና ቴሌቪዥኖችን አካቶ ነው የተሰራው፡፡ዋጋውስ ካሉ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ነው ተብሏል፡፡











