፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሐምሌ 17 2016| NBC ETHIOPIA-ዓለም አስደናቂ እና አስገራሚ ጉዳዮች በየጊዜያቱ እንካችሁ ማለቷን ቀጥላለች፡፡ በአየር ንብርት ለውጥ እየተፈተነች የምትገኘው ዓለም ፣የሙቀት መጠን መጨመር የዕለት ተዕለት ስጋት እንደሆነባት ቀጥሏል፡፡
በዚህ ጉዳይ ከሚፈተኑ ሀገራት አሜሪካ ዋነኛዋ ስትሆን በፍሎሪዳ ግዛቷ የሙቀት መጠን ከ38 ዲግሪ ሴልሽየስ በላይ ከፍ ብሏል፡፡ ዜጎችም የሙቀት መጠኑን ለመቋቋም የተቻለውን ሁሉ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ግርምት የጫረብን ጉዳይም ከዚሁ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ የፓልም ቢች የእንስሳት ፓርክ ሙቀቱ የሚፈትነው የሰው ልጅን ብቻ ሳይሆን እንስሳቶችንም ነው ሲል ተደምጧል፡፡
በፓርኩ ውስጥ ያሉ እንስሶቶችም በሙቀቱ ተጨንቀዋል ለዚህም መላ ዘይጃለሁ ማለቱ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ፓርኩ እንስሳቱ ሙቀትን እንዲቋቋሙ በበረዶ በተከተተበት ገንዳን ለማዘጋጀት ተገዷል፡፡ እንስሳቱ ራሳቸውን ቀዝቃዝ እንዲያደርጉ በረዶ በገንዳ ውስጥ ይሞላቸዋል፡፡

የእንስሳት ተንከባካቢው ማይክ ቴሬል ሁሉም እንስሶቶችን ከደቡብ ፍሎሪዳ የአየር ጸባይ ጋር የተላመዱ ቢሆኑም ልክ እንደ ሰው ልጅ በሞቃታማ ወቅት መቀዝቀዝን ይፈልጋሉ ለዚህ ነው ይህንን መንገድ የተጠቀምነው ብለዋል፡፡
እንደ ፍሎሪዳ ባሉ ሞቃታማ የአየር ጠባይ ባላቸው ስፍራዎች በበጋው ወቅት እንስሳቱ በሙቀት እንዳይሰቃዪ ታትረው እየሰሩም ናቸው፡፡በገንዳ ውስጥ ከበረዶ በተጨማሪ ምግብ ስለሚጨመሩላቸው ረዘም ላላ ሰዓት ገንዳ ውስጥ እንዲያሳልፉ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ ተግባር የእንስሳቱን የሙቀት መጠን ከ38 ወደ 23 C ማውረድ ተችሏል ብሏል ፓርኩ፡፡
ወደ ሌላኛው አስገራሚ ጉዳያችን አመራን፡፡ የማይክሮሶፍት መስራቹ ባለሀብቱ ቢል ጌትስ ቅቤን ከወተት ውጭ ማምረት የሚቻልበትን መንገድ ሊፈጥር መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ጉድ ሳይሰማ እንዲሉ ቅቤው የሚፈጠረው ከአየር እና ውሃ እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡

ሳቮር የተሰኘው ቅቤን ከአየር እና ውሃ እውን የማድረግ በካሊፎርኒያ በቢል ጌትስ የሚደገፈው ፕሮጀክት ከካርቦን ዳይኦክሳይድ እና ሃይድሮጂን ስብን የማምረት ዘዴ ነው ተብሎለታል፡፡
ሁሉም ቅባቶች የካርቦን እና የሃይድሮጂን ውህዶች ናቸው የሚለውን ሀሳብ እንደ መነሻ የወሰደ ስለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡ሳቮር ቅቤ እውን ከሆነም በቀጣይ እንደ አይብ እና አይስ ክሬም ያሉ ምግቦችን ከወተት-ነፃ በሆነ መልክ ማምረት የሚቻልበትን ሁኔታ እንደሚኖር ተነግሯል፡፡
ይህ የተቀነባበረ ስብ በተፈጥሮ ከእንስሳት ከሚገኘው ስብ በጣም ያነሰ የካርበን መጠን የሚኖረው ነው ተብሎለታል፡፡የሳቮር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ካትሊን አሌክሳንደር ሳቮር ቅቤ ልክ እንደ እውነተኛው ቅቤ በገበያው ላይ ለማቅረብ ረዥም ጊዜ አይወስደብንም፤ከእውነተኛው ቅቤ የተለየ ጣዕም የለውም ባይ ናቸው፡፡
ከወተት ተዋፅኦ የጸዳ ቅቤ እንዴት ያለ ይሆን የሚለው ጥያቄን የሚፈጥር ቢሆንም ተመራማሪዎቹ እንፈጥረዋለን ብለዋል፡፡
ከፍተኛ ምግብን በመመገብ እውቅና ያገኘችው የ24 አመቷ ቻይናዊት ከመጠን በላይ በመመገቧ ህይወቷ አልፏል፡፡ በርካቶች በኦላይን ከፍተኛ ምግብን እየተመገቡ የተመልካች ቁጥርን በማሳደግ እውቅናን የሚያገኙበት መንገድ ነው ሙክባንግ፡፡
ታዲያ ከዚሁ ጋር በተገናኘ የ24 ዓመቷ ቻይናዊት ፓን ሺያኦቲንግ በሙክባንግ ተመልካቾች ለማስደሰት ከፍተኛ መጠን ያለው ምግብ ከተመገበች በኃላ ለህልፈተ ህይወት መዳረጓ ተዘግቧል፡፡
ቻይና እ.ኤ.አ በ2020 በሙክባንግ ምግብን እየተመገቡ ለተመልካች መልቀቅ ትክክል አይደለም፤ የምግብ ብክነትም ያስከትላል በማለት እስከ 10,000 ዩዋን (1,400 ዶላር) ቅጣት እንዲጣል ውሳኔ ያስቀመጠች ቢሆንም በዚህ ተግባር የተሰማሩት ግን ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡
የሙክባንግ ቪዲዮች በእስያ ሀገራት ይበልጡ ተፋላጊ ሆነው ይታያሉ፡፡ቻይናዊት ፓን ሺያኦቲንግ በአስተናጋጅነት ስራ ላይ ተሰማርታ የቆች ቢሆንም በአቋራጭ ገንዘብ ለማግኘት ስራዋን በመተው በሙክባንግ ቪዲዮ ተቀላቅላ እይታን ለማግኘት ችላ ነበር፡፡
ከፍተኛ ምግብን እየተመገቡ ቪዲዮ በመስራት እውቅና ካተረፉት ተርታ ብትሰለፍም ለጤና እክል እና ለከባድ የሰውነት ክብደት ዳርጓት ቆይቷል፡፡ፓን በቀን በትንሹ ለ10 ሰአታት ያለማቋረጥ ምግብን መብላት ወይም አንድ በምትለቀው ቪዲዮዋ ከ10 ኪሎ ግራም በላይ የሚሆን ምግብ በመመገብ የተመልካች ቁጥሯን ከፍ አድርጋ ነበር፡፡
አተርፍ ባይ አጉዳይ ሆነና በስተመጨረሻ ግን የ24 ዓመቷ ወጣት እውቅናዋ ለምግብ መፈጨት ችግር አጋልጧት ለሞት አብቅቷታል ይላል የኦዲቲ ሴንትራል መረጃ ነው፡፡
በሙክባንግ ቪዲዮ ከፍተኛ ምግብን እየተመገቡ እይታ በመጨመር ገንዘብ የሚሰበሰቡ ሰዎች ከወጣቷ ህልፈት ትምህርት መውሰድ እንደሚገባቸው በአጽንኦት እየተገለጸ ነው፡፡ ነፍስ ይማር ነው እንግዲህ ሌላ ምን ይባላል::












