፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሐምሌ 11 2016| NBC ETHIOPIA-ሁላችንም ባንድም ሆነ በሌላ መንገድ ልዩ የሚያደርገን በርካታ ነገሮች አሉን፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ከአብዛኛው ሰው በተለየ ሁኔታ ልዩ የሚያደርጋቸው እና ያልተለመደ የሰውነት ክፍል እና ባህሪ አላቸው፡፡ በተፈጥሮም ይሁን በተለያዩ የጤና እክሎች እነዚህ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
እነዚህ ሰዎች ያላቸው የሰውነት ክፍል ምናልባትም ተጨማሪ የእጅ እና የእግር ጣቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ሁኔታም በአካል ላይ ሲከሰት ፖሊዳክ-ቲሊቲ በመባል ይታወቃል፡፡ሌላው ሰዎች ፕሮቲ-የስ ሲንድሮም በተባለ የዘረመል መታወክ ሲጠቁ ተጨማሪ የአጥንት እና የቆዳ እድገት ሊያስከትልባቸው ይችላል፡፡
የአብዛኛው ሰው የሰውነት ክፍል በተወሰነ መልኩ በጸጉር መሸፈን የተለመደ ነገር ነው፡፡
ለዩ ዜን – ሁዋን ግን ሁሉም ነገር የተለየ ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ደረጃ የሰውነቱ ክፍል በፀጉር የተሸፈነ ነው፡፡

ከ2 አመቱ ጀምሮ ዩ 96 በመቶው ሰውነቱ በፀጉር ተሸፍኗል፡፡ ለዚህም ባጋጠመው ያልተለመደ የጤና እክል ሳቢያ ነው፡፡ ይህም በዓለም ላይ በሰውነቱ ላይ እጅግ በጣም ብዙ ጸጉር ያለው ሰው የሚል ስያሜን አሰጥቶታል፡፡
በተለያዩ አውራ ጎዳናዎች ላይ ሲጓዝም አላፊ አግዳሚው ስልኩን አውጥቶ ይቀርጸዋል፡፡ አንዳንዶችም አብረውት ፎቶ ይነሳሉ፡፡ሰዎች አልወደውም ወይም ደስ አይለኝም ብለው በሚያስቡት የሰወነት ክፍላቸው በራስ መተማመናቸው ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ በተለያዩ ጊዜያት ሲገልፁ ይደመጣሉ፡፡
በዚህም መስተካከል አለበት ብለው በሚያስቡት የሰውነት ክፍላቸው ላይ ቀዶ ህክምና ሲያደርጉ እናስተውላለን፡፡ አንድ ግለሰብ ግን ተፈጥሮ የሰጠውን የፊት ገፅታ በጣም እንደሚወደው ይናገራል፡፡ አንድም ቀን ከሰው የተለየሁ ሆኛለው ብዬ ተሰምቶኝ አያቅም ይላል፡፡ መህመት ኦዚ-ዩሬክ::

መህመት በአሁኑ ወቅት 8 ነጥብ 80 በሚረዝመው አፍንጫው በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ሊያገኝ ችሏል፡፡ መህመት ኦዚ-ዩሬክ በጊነስ ወርልድ ሪከርድ ላይም የአለም የረጅም አፍንጫ ባለቤት ሲል በመዝገቡ አስፍሮታል፡፡
የትኛውም ስፍራ ስንቀሳቀስ ሰዎች በመገረም ትኩር ብለው ይመለከቱኛል የሚለው ቱርካዊው መህመት የሰዎች አስተያየት ምንም እንደማይመስለው እና ፈጣሪ በሰራው ነገር ሁሉ ደስተኛ እንደሆነ ይናገራል፡፡
ሲያጌጡ ይመላለጡ እንዲሉ በአለማችን ላይ በርካታ ሴቶች አርቴፊሻል ነገሮችን ፊታቸው ላይ ሲያደርጉ እናስተውላለን፡፡ ዘመን አመጣሽ ፋሽንን በመከተል ሂደትም በተፈጥሮአዊ ገፅታቸው ላይ ተጨማሪ ነገሮችን ሲያደርጉ ለጉዳት የሚጋለጡ ብዙ ናቸው፡፡
አንዳንዶች የአይን ሽፋሽፍትን በተፈጥሮ ነገሮች በመንከባከበ ለማሳደግ ሲጥሩ አንዳንዶች ደግሞ በአይን ሽፋሽፍት ላይ ተጨማሪ ቅጥያ ያደርጋሉ፡፡ ለዩ ጂያንሺያ ግን ተፈጥሮ አድሏታል፡፡

ጂያ-ንሺያ በሚያስደንቅ ሁኔታ በአለም ላይ ረጅም የተፈጥሮ ሽፋሽፍት ባለቤት ናት፡፡ የአይን ሽፍሽፍቶቿ 4 ነጥብ 88 ኢንች ወይም 12 ነጥብ 40 ሴ.ሜ ርዝማኔ አላቸው፡፡
ጂያንሺያ ከሰኔ 28 2016 ጀምሮ በጊነስ ወርልድ ሪከርድ ስር የረጅም ሽፋሽፍት ባለቤት በመሆን ተመዝግባለች፡፡ጂያንሲያ አንድም ቀን የማይመች ሆኖ አግኝታው እንደማታቅ እና ከብዙ ሴቶች በተለየ መልኩ ልዩ ውበት እንደሰጣት ትናገራለች፡፡
ሌላኛው አስገራሚ እና ልዩ የሆነ አካላዊ ባህሪ ያለው ሰው ጌሪ ተርነር ሲሆን ኤህለር-ዳንሎስ ሲንድሮም በተባለ ባልተለመደ የጤና እክል የተጠቃ ሰው ነው፡፡

በዚህም ሳቢያ የተርነር የሰውነቱ ቆዳ እንደፈለገው እንዲለጠጥ አድርጎታል፡፡ በሆዱ ላይ ያለው ቆዳ ወደ 6 ነጥብ 2 ኢንች ወይም 15 ነጥብ 8 ሴ.ሜ ርዝመት ሊዘረጋ ይችላል፡፡












