፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 21 2016| NBC ETHIOPIA-በአማራ ክልል የክልል እና የዞን ከፍተኛ መሪዎች በወቅታዊ የፖለቲካ፣ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ዙሪያ እመከሩ ነው።
በምክክር መድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የምክክር መድረኩ ከሰሞኑ የተካሄዱ ውይይቶችን ለማጠቃለል እና የቀጣይ ሥራዎችን አቅጣጫ ለመስጠት መሆኑን ገልጸዋል።
የገጠሙ ችግሮችን በውይይት እና በድርድር ለመፍታት ምላተ ሕዝቡን ያሳተፈ የሰላም ውይይት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር አካሂደናል ብለዋል። በውይይቱ የመከላከያ መሪዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውንም አስታውሰዋል። የተደረገው ውይይትም ጥሩ ቁምነገር የተገኘበት እንደነበር ርእሰ መሥተዳደሩ ተናግረዋል።
በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ከትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችን ለመፍታት ጥረት እየተደገ መኾኑንም ገልጸዋል። የቆዩት እና አዳዲስ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች ተባብረው መሥራትን የሚጠይቁ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

በግጭቱ የትምህርት ሥራ በእጅጉ መጎዳቱን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ በትምህርት ዙሪያም መወያያታቸውንም ተናግረዋል። የማይማሩ ተማሪዎች እና የማያስተምሩ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ገልጸዋል። በትምህርት የደረሰው ጉዳት ወደፊትም ተጽዕኖው ከፍ ያለ መሆኑን ነው የተናገሩት። ከሰሞኑ በተደረጉ ውይይቶች የግብርና እና ጤና ሥራዎችን በተመለከተ መወያያታቸውንም አመላክተዋል።
በ2016 በጀት ዓመት ክልሉ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ማለፉን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ለ2017 ዓ.ም በሚገባ መዘጋጀት ይጠበቅብናልም ብለዋል።
እያንዳንዳችን አሁን ያለውን ችግር ሊያሻግር የሚችል ሥራ መሥራት አለብን፤ ቢያንስ ቢያንስ ችግሮችን ከሚያባብሱ ሥራዎች መቆጠብ አለብን ብለዋል። ለጋራ ችግራችን መረባረብ እና በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ችግሮቻችንን በመቁጠር የትም ልንደርስ አንችልም፤ ለውጥም አይመጣም ብለዋል።

በአንድነት መሥራት ከተቻለ በክልሉ ከፍተኛ አቅም አለ ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ግልጽ አቋም ይዞ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል። የሚዋዥቅ አቋም እና አመለካከት መያዝ እንደማይገባም አስገንዝበዋል።
ካልተባበርን እና አንድ ካልሆን ጊዜውን ማለፍ አንችልም፤ ውይይቱ በጋራ ተግባብተን መሥራት እንድንችል የሚያደርግ መሆን ይገባዋልም ብለዋል። ሕዝብን ከችግር የሚያወጣ ሥራ መሥራት ይገባልም ብለዋል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCEthiopiaSC
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












