፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 17 2016| NBC ETHIOPIA- “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል ክልላዊ የሰላም ኮንፈረንስ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በኮንፈረንሱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ባስተላለፉት መልዕክት በህዝብ ትግል የመጣው ለውጥ ለሀገርና ህዝብ ያስገኛቸው በርካታ ትሩፋቶች አሉ ብለዋል።
ለውጡ ፍሬ አፍርቶ የአገራችን እድገትና የህዝባችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በዘላቂነት እንዳይረጋገጥ ተግዳሮት አጋጥሟል ሲሉ ተናግረዋል።
የዚህ ኮንፈረንስ ዋና ዓላማም ሰላምን ማምጣት ነው፤ ሰላም እንዲመጣ በጥፋት መንገድ እየተጓዙ ያሉ አካላት ወደ ሰላም መምጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
አገራችን የፌደራሊዝም ስርዓት የሚተገበርባት የበርካታ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር በመሆኗ በምንም መንገድ ፍላጎትን በሃይል መጫን እንደማይቻል መገንዘብ እንደሚገባ አስረድተዋል።
ችግሮችን በውይይትና በንግግር ለመፍታት በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልጸው፤ የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎችም ይህንን በመገንዘብ የሰላምን ጥሪ መልዕክት በመያዝ ችግር ውስጥ የገቡትን መመለስ እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው፤ ኮንፈረንሱ የችግሩን መንስኤ፣ ያስከተለውን ጉዳትና በቀጣይ መወሰድ ባለባቸው መፍትሄዎች ላይ እንደሚመክር ተናግረዋል።
ይህም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስችሉ ስልቶችን በመዘየድ ችግር ውስጥ የገቡትን ወደ ሰላም ለማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም እንዲሁ።የክልሉ መንግስት በኮንፈረንሱ የተገኙ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለመተግበር ቁርጠኛ አቋም አለው ሲሉ ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የሰላም ኮንፈረንስ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራር አባላት፣ ከሁሉም የክልሉ ዞኖች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












