፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 13 2016| NBC ETHIOPIA- የምሽት ንግድ፤ ግብይት ወይንም አገልግሎት ጅማሮውን ያረገው በቻይና በመካከለኛው ክፍለ ዘመን እንደነበር ይነገራል፡፡
ታዲያ ጅማሮውን በቻይና ያድርግ እንጂ ቀስ በቀስ አብዛኛው የአለም ሀገራት ይህን ባህል በመከተል አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን 24 ሰዓት አገልግሎት የመስጠት ባህልን አጧጡፈው ቀጥለውታል፡፡
ሁነቱ በየሀገሬው የሚኖሩ ህዝቦችን ፍላጎት በማንኛውም ሰአት ለማሟላት ከማስቻሉ በላይ የስራ ባህል በእጅጉ እንዲዳብር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ይገለፃል፡፡
በአለማችን ላይ 24 ሰዓት ሙሉ አገልግሎት በመስጠት ትልልቅ ገበያን ከመሰረቱ ሀገራት መከካል ጥቂቱን እንንገራችሁ፡፡
1. ቻይና ሆንግ ኮንግ

ቴምፕል የጎዳና ገበያ…. በጎዳዎች ላይ የጦፈ የምሽት ግብይት በብዛት ከሚስተዋልባቸው ሀገራት መካከል አንዷ በሆነችው እና የምሽት ገበያ ጀማሪ መሆኗ በሚነገርላት ሀገረ ቻይና ሆንግ ኮንግ ነው መገኛውን ያረገው፡፡
ይህ ገበያ ከሀገሬው ሰዎች ባሻገር በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ቱሪስቶች መዳረሻም ጭምር ነው፤ጅማሮውን ካደረገ ዘለግ ያለ አመታትት ባስቆጠረው በዚህ ቴምፕል የጎዳና ገበያ ፈልገው የሚያጡት ነገር የለም ማለት ያስደፍራል፡፡
የቻይውያን ባህላዊ ፈጣን ምግቦች፤ ፍራፍሬዎች፤ ዘመናዊ እና ባህላዊ አልባሳት፤ ካፌ እና ሬስቶራንቶች፤ ኤሌክትሮኒክስ ፤የቻይናውያን እደ ጥበባትን ጨምሮ ሌሎችም በዚህ ገበያ ተፈልጎ አይታጣም፤
ይግረሞት እንዲሉ ደግሞ በዚሁ ስፍራ አገልግሎት ከሚያቀርቡ ተቋማት እና ድርጅቶች ባሻገር እጣ ፈንታ ነጋሪዎች መዳፍ አንባቢዎች እና በርካታ የኦፔራ ተጫዋቾችን ትርኢት የሚያሳዩ ወጣቶች በዚሁ ስፍራ መመልከት የተለመደ ነው፤
24 ሰአታትን በስራ ማሳለፍ ባህል በሆነባት ቤጂንግ ይህ የምሽት ገበያ ብርቅ እና ድንቅ ሳይሆን የግዴታ በመሆኑም በየእለቱ በእኩለሊት እንኳን ሳይቀር ሞቅ ያለ እንቅስቃሴን መመልከት የተለመደ ነው፡፡ታዲያ ቀኑን በተለያዩ ተቋማት ላይ ተቀጥረው ሲሰሩ የዋሉ ዜጎች ለቤታቸው ብሎም ለሚፈልገሁት አገልግሎት ግዢን ለመፈፀም ገበያ ይዘጋብኝ ይሆን የሚል ስጋት የለባቸውም በተመቻቸው ሰዓት ለሊቱን ሙሉ የሚሰተናገዱበት ገበያ አላቸው፡፡
2. ሞሮኮ ማራካሽ

በሰሜናዊቷ የአፍሪካ ሀገር ሞሮኮ ማራካሽ ውስጥ እንዲሁ ጸሀይ አትጠልቅም አይተኙም እንዴ የሚያሰኝ ሰፊ የምሽት እንቅስቃሴ በገበያ ስፍራዎች መመልከት የተለመደ ነው፤
ጸሀይ ከአድማስ በታች ስትጠልቅ የማራካሽ የምሽት ገበያ እንቅስቃሴው መጧጧፍ ይጀምራል፤ ቅመማ ቅመሞች አየሩን በሚያስደንቅ መአዛ ያውዱታል፤ ቀለማት ባላቸው መብራቶች ያሸበረቁት ድንኳኖች ወደ ሌላ ሊጓዝ የፈለገን እግር ሁሉ ጠምዝዞ ወደ እኔ ኑ የሚያሰኝ ሀይል አላቸው ይላሉ ወደ ስፍራው ያቀኑ እና የምሽት ገበያውን የተመለከቱ ቱሪስቶች
በስፍራው በአብዝኛው ፋስት ፉዶች እንዲሁም የሞሮኮአውያ እና የሌሎች ሀገራ ምግቦች በስፋት ይሸጡበታል፤
አገልግሎቱንም ለማግኘት ከጀንበር መግቢያ አንስቶ እስከ እኩለ ለሊት ማብቅያ ድረስ በርካቶች በስፍራው ይንቀሳቀሱበታል፡፡
በማራካሽ በየአመቱ ከሚመጡ 2 ሚሊየን የሚልቁ ቱሪስቶች አብዣኞቹ ይህንን ስፍራ በተደጋጋሚ ሳይጎበኙ አይመለሱም፡፡
3.ቱርክ ኢስታንቡል

የቱርካውያን ታላቅ ከተማ በሆነችው ኢስታንቡል ውስጥ ለበርካታ መቶ አመታት ጎብኒዎችን ሲማርክ የቆየ አንድ ስፍራ አለ….. ግራንድ ባዛር
ግራንድ ባዛር በአለም ላይ ካሉ እጅግ ጥንታዊ እና ትልቅ ገበያ ስፍራዎች መካከል አንዱ ነው፤በእንቅስቃሴ የተጨናነቁ ከ 4ሺ የሚልቁ ሱቆች እና ድንኳኖች በውስጡ ያያዘው ስፍራው 30ሺ 700 ካሬ ስፋት ላይም ይገኛል፡፡
ግራንድ ባዛር በየእለቱ ከ250 ሺ እስከ 400ሺ ያህል ሰዎች የሚጎበኙት ሲሆን ጀንበር በዚህ ስፍራም አትጠልቅም፡፡
ምጣፎች ፤ባህላዊ እና ዘመናዊ አልባሳት፤ ጌጣጌቶች፤ የቤት ውስጥ እቃዎች እና ሌሎች በርካታ ቁሳቁሶችን በውስጡ ይዟል፤
ከገበያ ስፍራነቱ ባልተናነሰ መልኩ በኢስታንቡል ውስጥ ካሉ የቱሪስት መዳረሻች መካከል አንዱ እና ዋነኛውም በመሆን ለአገሪቷ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ያስገኛል፡፡
4. ማሌዢያ ቡኪንት ቢንታግ

ከምሽት 11 ሰአት በኋላ ይበልጡኑ እየደመቀ እንደሚሄድ የሚነገርላት ገበያ ካላቸው ሀገራት መካከል ማሌዢያ ሌላኛዋ ናት፡፡
በማሌዢያ በቡኪንት ቢንታግ አካባቢ የሚገኘው የጎዳና ላይ የምሽት ገበያ ጃላን አሎር የሚል መጠሪያም አለው
ይህ የጎዳና ላይ ገበያ ይበልጥ በሚሸጧቸው የምሽት ምግቦች እውቅናን ማግኘት ችሏል፤በማሌዢያ ባህላዊ ምግቦች፤ ኑድል፤ የባህር ምግቦችን የሚሸጡ በርካታ ድንኳኖች እኩለ ለሊቱን ሲሸጡ በሚያድሩበት በዚህ ገበያ ስፍራ በተደረደሩ የፕላስቲክ ወንበሮች ተቀምጠው ለሊቱን ሙሉ የሚያወጉ ሰዎችም መመልከት የተለመደ ነው፤
ለአካባቢው ነዋሪዎች ምግብን በፈለጉት ሰአት ወደ ጎዳናው ጎራ ብሎ ከማግኘት አንስቶ ጎብኚዎች በቀላሉ የሀገሪቱን ባህላዊ ምግቦች በአንድ ስፍራ እንዲያገኙም አስችሏቸዋል፡፡
5. ስፔን ማድሪድ

ሜርካዶ ዴ ሳን ሚጌል ገበያ በስፔን በማድሪድ እምብርት ላይ የሚገኘው ይህ የገበያ ማዕከል ከ 100 አመታት በላይ እንዳስቆጠረም ይገለጻል፤
በማድሪድ ካሉ በርካታ ውብ የቱሪስት መስህቦች መካከል አንዱም ነው ፤ይህ የገበያ ስፍራ ሁሉም ተወዳጅ የሆኑ የስፔን እና የሌሎች ሀገራት ምግቦች የማይታጡበት ሰፊ የገበያ ስፍራ ነው፤
ወደ ማድሪድ የሚያቀኑ ብዙዎችም ይህን ስፍራ የረገጠ እና በምሽት ያለውን ድባብ በሰፊው የተመለከተ ሰው ደጋግሞ ወደ ስፔን ይመላለሳል ይላሉ፤
መሰል ሰፊ የገበያ ማዕከላት ድምቅ ያለ የምሽት አግልግሎት ሲሰጡ ማስተዋል እምብዛም በሀገራችን ባይስተዋልም የሰው ልጆች ፍላጎት ቀን እና ሌት ሙሉ ነው እና ቢለመድ የሰዎችን ፍላጎት ከማርካት ባለፈ የስራ ባህልን ያበረታታል፤ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ያመጣል ለቱሪስቶችም መስብ ይሆናል ጥቆማችን ነው፡፡
በ-የአብስራ ሚሊዮን












