፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 11 2016| NBC ETHIOPIA-አመታትን ባስቆጠረ የእርስ በእር ጦርነት መቶሺዎች ለሞት ተዳርገዋል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿ ተፈናቅለዋል ፡፡ በጎሳ ግጭት እና በሰብአዊ ቀውሶች አስከፊ ታሪክ ያላት የምእራብ ሱዳኑዋ ዳርፉር ግዛት ፡፡
ዳርፉር እ.ኤ.አ. በ2000ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት እና ለሚሊዮኖች መፈናቀል ምክንያት የሆነ አስከፊ ግጭት አጋጥሟት እንደነበር የሚታዎስ ነው ፡፡
ታዲያ ዛሬ ላይ ዳርፉር ያለፈውን አስከፊ ታሪኳ ረስታ እንደ አዲስ ወደ ሌላ የዘር ማጥፋት ወንጀል እያመራች ነው ሲል cnn ባወጣው መረጃ አመላከቷል ፡፡
የሱዳን ጦር እና የፍጥኖ ደራሽ ኃይሉ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከገቡ 14 ወራትን አስቆጥረዋል ፡፡ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ በዳርፉር ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግድያዎች ተባብሰዋል። በግጭቱም ከ14,000 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን እና ከ8 ሚሊየን በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት አመላክቷል ፡፡
ሁለቱ ሀይሎች ግዛቶችን ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ፍልሚያ አሁን ላይ ወደ ኤል ፋሸር ተዘዋውሯል ፡፡ ግዛቷ የቀናት ጉዳይ እንጂ በመሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ መራሹ ፈጥኖ ደራሽ ሀይል እጅ ልትወድቅ እንደምትችልም ተንታኞች ከሰሞኑ ያስታወሱት ከዚህ አንጻር ነው ፡፡
የጅምላ ጭፍጨፋ ፣ ጾታዊ ጥቃት እና የመንደሮችን ውድመትን ጨምሮ መጠነ ሰፊ ግፍ እና ከዘር የማጥራት ዘመቻዎች ጋር የተገናኙ የመብት ጥሰቶችን መፈጸማቸው ሂዩማን ራይትስ ዎች እና ሌሎች ድርጅቶች ገልጸዋል ፡፡

ባለፈው ወር ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ኤል ፋሸርን መክበቡን ተከትሎ ቢያንስ 134 የከተማዋ ነዋሪዎች ተገድለዋል ፡፡
በአሁን ወቅት በዳርፉር የተፈፀመው ጥቃት ዒላማ የተደረገበት ሁኔታ ፣ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ስልታዊ አካሄድ እና በአካባቢው ያሉ የጎሳ ግጭቶች እንዲሁም ቀድሞ የነበረው ታሪካዊ ቁርሾ ዳርፉር ወደ ሌላ አስከፊ የዘር ማጥፋት እየተሻገረች እንደሆነ ማሳያዎች ናቸው ይላሉ ተንታኞች ፡፡
በአሁን ወቅት እየተፈፀመ ያለው ግፍ በአብዛኛው በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ በነበረው የእርስ በእርስ ግጭት ተሳታፊ የነበሩ ሀይሎች የሚሳተፉበት ነው ፡፡
ተመሳሳይ የጦር አዛዦች፣ ተመሳሳይ ጎሳዎች እና በዳርፉር የሚገኙ ተመሳሳይ የተጎጂ ቡድኖች (አረብ ያልሆኑ ማህበረሰቦች) በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑ ሌላኛው ማሳያ ነው ይላሉ ፡፡
2 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የሚኖሩባት ኤል ፋሸር ማሳሊትን ጨምሮ አረብ ያልሆኑ ብሄረሰቦች በብዛት ይኖሩበታል ። ከተማዋ ባለፈው አመት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አረብ ያልሆኑ ሰዎች የተገደሉባትን ኤል ጂኒናን ጨምሮ ከሌሎች የዳርፉር አካባቢዎች የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን አስጠልላለች ።

በዚም የተነሳ ኤል ፋሸር በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ቁጥጥር ስር ከገባች ተመሳሳይ ግፍ ሊፈጸም ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል ፡፡
ግጭቱ ንጹሃን ላይ እያደረሰ ካለው ጉዳት አንጻር እያገኘ ያለው ዓለም አቀፍ ምላሽ በቂ አይደለም ተብሎ እየተተቸ ይገኛል ፡፡ በሱዳን ጦር ሃይሎች እና ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተደረጉ አለም አቀፍ ጥረቶች አለመሳካታቸው የሚታወቅ ነው ። ምዕራባውያኑም ቢሆኑም ዜጎቻቸውን ከሱዳን ካስወጡ በኋላ ሱዳንን ጉዳይ ችላ ብለውታል በሚል ይወነጃጀላሉ፡፡
የሱዳን ጦርነት ከሌሎች አለም አቀፍ ግጭቶች ጋር ሲወዳደር በቂ ሽፋን እንዳልተሰጠው የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጠበቃ ዮናህ ዳይመንድ ተናግሯል።
ሰላማዊ ዜጎችን የሚጎዳ፣ በሚሊዮኖች ላይ የረሃብ ሞት የሚያስከትል ግጭት እና እየተካሄደ ያለው የዘር ማፅዳት ተመሳሳይ ትኩረት የማይሰጥበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል።
ይህ ትኩረት እጦት ሰብአዊ ጥረቶችን እንደሚያደናቅፍ ጠቁመው ጋዛ እና ዩክሬን እያንዳንዳቸው 30 በመቶ የሚሆነውን የሰብአዊ ድጋፍ ምላሽ እቅዳቸውን ሲያሳኩ 25 ሚሊዮን ህዝብ አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልገው ሱዳን ከዚህ ገንዘብ ግማሽ ያህሉን ብቻ እንዳገኘ ጠቁመዋል።
አሜሪካ ፣ እንግሊዝ እና ሌሎች ሀገራት ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ የዘር ማጥፋት ዘመቻን እንዲያቆም በአጋራቸው በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚያስችል አቅም አላቸው ብለዋል። በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በሱዳን ካለው ጦርነት ጀርባ አለች መባሉ የሚታዎስ ነው፡፡
የሱዳን ጦረ በአብደል ፈታህ አልቡርሃን በመመራት በሌላ በኩል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ጦርነት ውስጥ ከገቡ ዓመት አልፏቸዋል፡፡
በ-የአብስራ ብርሃኑ












