፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 11 2016| NBC ETHIOPIA-በአቶ አደም ፋራህ የተመራው የልዑካን ቡድን ከሰኔ 9 እስከ 12/2016 በሚካሄደውና ዎርልድ ማጆሪቲ ፎር መልቲፖላር ኦርደር በሚል መሪ ቃል በሩሲያ ቪላዲቮስቶክ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም ላይ እየተሳተፈ ነው።
“ኃላፊነት የተሞላበት የመረጃ ስርጭት ፍትሐዊ የዓለም ስርዓትን ከመገንባት አንጻር” በሚል ርዕስ በተስተናገደው የፎረሙ ክፍል ላይ ንግግር ያደረጉት በብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በንግግራቸው የኢትዮጵያ የዲጂታል ፖሊሲ የዜጎችን ብዝሃነት ታሳቢ ያደረገ ሁሉንም ማህበረሰብ ያማከለ እና የወደፊቷን ዲጂታል ኢትዮጵያ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ አዲሱ አክለውም በአሁኑ ወቅት ያልተረጋገጠ የተዛባና ሃሰተኛ መረጃ ሃላፊነት በጎደለው መልኩ በፍጥነት የሚሰራጭበት ሁኔታ እየታየ ነው ብለዋል።

የዚህ ዓይነቱን ችግር ለመቋቋም ቴክኒካዊ መፍትሔ ብቻ ሳይሆን ዘመኑን ታሳቢ ያደረገ የሚዲያ ባህርያት የመረዳት ባህል ሊዳብር እንደሚገባም አስረድተዋል። በዚህም ለእውነት፣ ለትክክለኛነት፣ ለታማኝነትና ለግልጽነት ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
አቶ አዲሱ እነዚህን የድህረ እውነት ዓለም ፈተናዎች ለመቋቋም ካቀረቧቸው ሃሳቦች መካከል ሕዝቡ የሚሰራጩ መረጃዎችን ትክክለኛነትና የመረጃ ምንጩን ተቀባይነት እንዲያጣራ ማስተማር ቀዳሚው መሆኑን ተናግረዋል።
ሃሳብን በነጻነት የመግለጽን መብት ባከበረ መልኩም ሃሰተኛ የመረጃ ስርጭቶችን መከላከል የሚያስችል የተጠያቂነት የሕግ ማዕቀፎችን ተግባራዊ የማድረግን አስፈላጊነትም አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በመንግስትና መረጃን በማጣራት በተሰማሩ አካላት መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር የሃሰተኛ መረጃዎችን ስርጭት ተከታትሎ ማጋለጥ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
የተሻሉ ተሞክሮዎችንና ፈጠራዎችን በማጋራት፣ እድገትን፣ ደህንነትን እና መረጋጋትን የሚያበረታታ ጠንካራ ዲጂታል አካባቢ መፍጠር እንደሚቻልም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከብሪክስ ጋር በጋራ በመስራት የዲጂታላይዜሽንን የለውጥ አቅም ለመጠቀም ቁርጠኛ መሆኗን የገለጹት አቶ አዲሱ በጋራ ፍትሃዊ ፣ አካታችና ስኬታማ አለምን እንገንባ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
????YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
???? TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
????Website – https://nbcethiopia.com/news/
????Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት












