፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 06 2016| NBC ETHIOPIA-ጥቂት በግንብ ከታጠሩ ከተሞች ውስጥ አንዷ ናት ፡፡ ባሏት የስነ ምድር ምርምር ስፍራዎች እና የባህር ዳርቻዎቿ የበርካታ ጎብኚዎችን ቀልብ ትገዛለች ፡፡ የሜክሲኮዋ ቱሌም ከተማ ፡፡
ከተማዋ ከ820 አመታት በፊት በማይውያን ስልጣኔ እንደተገነባች ይነገራል ፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በእስፓኒሽ ወረራ ምክንያት ከተማዋን የመሰረቷት የማይ ህዝቦች ለቀው እንደወጡ እና ለበርካታ አመታት ተረስታ ከቆየች በኋላ በ1840 ፍሬድሪክ እና ጆን ሎይድ በተባሉ ግለሰቦች ምክንያት ዳግም እንደተገኘች መረጃዎች ያሳያሉ ፡፡
ለብዙ ግዜያት ከሩቅ ቦታዎች ለሚመጡ እና ለአካባቢው ሰዎች እንደ ዋና የንግድ ጣቢያ ሆና አገልግላለች። ጥጥ፣ካካኦ ፣ትምባሆ እንዲሁም ለሌሎች በርካታ ነገሮች በስፋት ይነገድባት እንደነበር ይነገራል ፡፡
ጥንታዊ ታሪኳ እና አሁን ላይ ያላት ውብ ድባብ ተጣምረው በበርካቶች ዘንድ ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን አድርገዋታል፡፡ ከተማዋ በሜክስኮ በብዛት ከሚጎበኙ ስፍራዎች ቀዳሚውን ቦታ ትይዛለች ፡፡
ከመዝናናት ባለፍ ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በአርኪኦሎጂ ስፍራዎቿ በታሪክ አድናቂዎች ዘንድ ከምንግዜውም በላይ ተወዳጅ እየሆነች መታለች።
ከአሰልቺ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ዞር ብሎ በሞቃታማ ገነት ውስጥ ለማሳለፍ ለሚፈልግ ጎብኚም ቀዳሚ ምርጫ ናት ፡፡
ወደ ቱሌም ከተጓዙ ከአስገራሚ ተፈጥሯዊ ጸጋዋ ጀምሮ አዲስ የሚታይ እና የሚከወን ነገር አያልቅም ይባላል፡፡ ቱሌም በቀድሞ ዘመን የንግድ ማዕከል ከመሆኑዋ በተጨማሪ የማያውያን የአምልኮ ስፍራ እንደነበረች በከተማዋ በቀድሞው ዘመን የተገነቡት ቤተ መቅደሶች እና በተለያዩ ስፍራ በግንቦች ላይ የተቀረጹት ምስሎች ያስረዳሉ፡፡

በከተማዋ ከ60 በላይ ጥንታዊ ህንጻዎች ሲኖሩ ኤል ካስቲሎ ፣የፍሬስኮስ ቤተ መቅደስ እና Descending God ይተሰኙት ደግሞ በጥብቅ ከሚጠበቁት ውስጥ ናቸው ፡፡
ቱሌም ለጎብኚዎች ምቹ ከመሆኑዋም ባሻገር የበርካታ እንስሳት መኖሪያ ናት ፡፡ በጥቂት ቦታዎች ብቻ የሚገኘው ጃጉዋርን ጨምሮ ፣ኤሊ፣ ጦጣ፣ አጋዘን ፣ፓሮት እና የተለያዩ እንስሳት መኖሪያ ናት፡፡
ከቱሌም ከተማ ወጣ ብሎ በደን ውስጥ የሚገኘው አዙሊክ ኡህ ሜይ ወይም የጥበብ ከተማ ሙዚየም ለጥበብ ሰዎች እና ለሀሳብ ፈጠራ ምርጡ ስፍራ ነው ፡፡
ወደ ቱሌም የተጓዘ ጎብኚ በተንጣለለው እና በማራኪው ባህር ዳርቻ መዝናናት ፣ በውሃ ላይ የሚከወኑ ስፖርታዊ መዝናኛዎች እና በከተማዋ የሚገኘውን ትልቅ ፒራሚድ መውጣት ሊዝናኑባቸው የሚችሉበት ጥቂት ስፍራዎች ናቸው፡፡
Playa Paraiso ፣Play Ruinas እና አኩማል በቱሌም ከሚገኙ ውብ የባህር ዳርቻዎች ውስጥ የተወሰኑት ናቸው፡፡ ታዲያ ይችን በተፈጥሮ ጸጋ እና በሰው ሰራሽ ታሪክ የበለጸገች ከተማን ለመጎብኘት ህዳር እና ታህሳስ ተመራጭ ወቅት ነው ፡፡

በአሁን ወቅት በየጊዜው ወደከተማዋ የሚጓዙ ጎብኚዎች ቁጥር ከምንግዜም በላይ እየጨመረ ነው ፡፡ በአመት በአማካኝ ከ 2 ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ እንደሚጎርፉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በ-የአብስራ ሚሊዩን












