፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 06 2016| NBC ETHIOPIA- ይህ የምትመለከቱት በበሪ እና በሰው መሃል የሚደረግ ትንቅንቅ ነው፡፡ጅማሮውን ያደረገው በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሰሜን ምስራቅ ስፔን እንደሆነ ይነገራል፡፡ በቀደመው ጊዜ በሀገሬው ይኖሩ የነበሩ የጥንት ስፔናውያን የአምልኮ ስርአት ጋር ግንኙነት እንዳለውም ታሪክ ያወሳል……የቡል ፌስቲቫል
በፈረንጆቹ 1592 አካባቢ ይከበርበት ከነበረው መስከረም ወር በስፔን በዚሁ ወር በሚኖረው የአየር ንብረት ሳቢያ እስካሁንም ወደ ሚከበርበት ወርሀ ሀምሌ ሊሸጋገር ችሏል፡፡
በመካከለኛው ክፍል ዘመን ይህንን ስርአት ጥንታዊ ስፔናውያን በወቅቱ ይከተሉት ከነበረው አምልኮታዊ ስርአት ጋር ግንኙነት እንዳለው አንዳንድ ጸሃፈት ይጠቁማሉ፡፡
ፌስታ ዲ ሳን ፈርሚን ወይንም ሳን ፈርመን በተሰኘው አመታዊ ፌስቲቫል ሰሞን የሚከወነው የቡል ፌስቲቫል ከሀምሌ 6 እስከ 14 ባሉት ቀናትም በፓምፕሎና ስፔን ውስጥ በድምቀት ይካሄዳል፡፡

ጅማሮውን ባደረገበት በሀገረ ስፔን ኢንሴራር የሚል መጠሪያ ያለው ይህ የቡል ፌስቲቫል ጅማሮውን በሀገረ ስፔን ያድርግ እንጂ አሁን ላይ የብዙዎች አመታዊ ፌስቲቫል ለመሆን በቅቷል፡፡
በዚህ ፌስቲቫል ላይ በየጊዜው እየተጨመሩ ከሄዱ የመንገድ ላይ ትርኢቶች ባሻገር ለበአሉ መከበር ዋነኛ ምክንያት የሆነው የቡል ጨዋታ ወይንም ከተዋጊ በሬዎች ጋር የሚደረገው ትንቅንቅ የፌስቲቫሉ ውበት በመሆን እስከዛሬ ድረስ ሊዘልቅ ችሏል፡፡
በዚህ ፌስቲቫል 6 አንዳንዴም 10 የሚሆኑ ተዋጊ በሬዎች በማዘጋጀት እና ተጫዋቾችን ወይንም የፌስቲቫሉ ታዳሚዎችን ነጭ እና የተዋጊ በሬዎችን ቀልብ የሚስበውን ቀይ ልብስ በመልበስ ከተዋጊ በሬዎቹ ከፊት ለፊት በማስቀደም በታጠረላቸው ቀጭን መንገድ ላይ ከሞት እና ከአካል ጉዳት ጋር በፍቃድ ላይ የተመሰረተ ትንቅንቆሽ ውስጥ ይገባሉ፡፡
ይህንን ሁነት ለመታደም በየአመቱ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ወደ ሀገሪቱ የሚጎርፉ ሲሆን በውድድሩ ላይም ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፉበታል፡፡
እራስን የማትረፍ ሩጫ ውስጥ የሚፈጠር የአሸናፊነት እና የጀግንነት ስሜትን በውድድሩ ተሳታፊ ለሆኑ ሰዎች ሲያጎናጽፍ ለአንዳንዶች ደግሞ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሲሉ ይተቹታል፡፡

በየአመቱ በውድድሩ ተሳታፊ ከሚሆኑ ሰዎች 3 በመቶ የሚሆኑት በጨዋታው ወቅት በሚፈጠሩ ግፊያዎች፤ መረጋገጦች እንዲሁም ተዋጊ በሬዎቹ በሚያደርሱት ጉዳት ከቀላል እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳትን ያስተናግዳሉ፡፡
ከዛም ባሻገር ፊስቲቫሉ በየጊዜው የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች ከሰዎች እንዲሁም እንስሳት ሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር ተያይዞ ክሶችን ያቀርቡበታል፡፡
ነገር ግን አዘጋጆቹም ሆነ ለውድድሩ ልዩ ትኩረት እና ፍቅር ያላቸው ተሳታታፊዎች ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ውድድሩን አሁንም ድረስ ቀጥለዋል፡፡
ተሳታፊዎች ወደ ጨዋታው ከመግባታቸው አስቀድሞ ሊከተሏቸው የሚገቡ በርካታ ህጎች ያሉት የጨዋታ አይነት ሲሆን ወደ ጨዋታው ከመግባት አስቀድሞ መጠጥ መጠጣት፤ በውድድሩ ወቅት ሰልፊ መነሳት ሌሎች መሰል ድርጊቶች የሚከለክል የጨዋታ ህጎች አሉት፡፡
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት እንዳይከናወን ተከልክሎ የነበረው የቡል ፌስቲቫል በፈረንጆቹ 2022 ማለትም ከኮሮና ወረርሺኝ በኋላ ዳግም ሲከወን ግን ከ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ላይ ሰዎች ወደ ስፔን በማቅናት ተሳታፊ ሆነውበታል፡፡
በ-የአብስራ ሚሊዮን












