፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 04 2016| NBC ETHIOPIA- አይታና ትባላለች ነዋሪነቷ በስፔኗ ባርሴሎና የሆነ ባለሮዝ ቀለም ጸጉር የ25 ዓመት ወጣት ናት፡፡ በሙያዋ ደግሞ ሞዴል፡፡ ሞዴልነቷ በወር እስከ አስር ሺህ ዩሮ ገቢ ያስገኝላታል፡፡ በማህበራዊ ትስስር ገጽ አካውንቶቿ በየቀኑ ከዝነኛ እስከ ነጋዴ የእራት ግብዣ ጥያቄዎች ይጎርፉላታል፡፡
ሰውነቷ አንዳች ጥርጣሬን የማያጭርው አይታና ብዙዎች ማመን ቢያዳግታቸውም የሰው ሰራሽ አስተውህሎት ውጤት ናት፡፡ለሃገሯ ስፔን የመጀመሪያዋ የሰው ሰራሽ አስተውህሎት ሞዴል፡፡
የተፈጠረችው ዲዛይነሯና የክሉ ለስ ኤጀንሲ መስራች ሩበን ክሩዝ ድርጅቱ ደንበኞችን ማፍራት ባቃተውና ከባድ ጊዜያትን እያሳለፈ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ ድርጅቱ አቅሙን አሟጦ የተለያዩ ዲዛይኖችን ቢሰራም ደንበኛ ማፍራታ ላይ የነበረው ክፍተት ግን ተገቢውን ገቢ እንዳያገኝ እንቅፋት ፈጥሮበት ቆይቷል፡፡ እናም ተጽዕኖ መፍጠር የምትችል አንድ ሞዴል ለመፍጠር አሰበ፡፡አስቦም አልቀረ የሰው ሰራሽ አስተውህሎት ሞዴሏ አይታና ተፈጠረች፡፡

ምናባዊ ሞዴሏ አይታና መልኳ ለሰው ልጅ ፍጹምነት የቀረበ ነው፡፡ በወር እስከ 10 ሺህ ዩሮ ታገኛለች ፡፡ አነሰ ቢባል 3 ሺህ ዩሮ። በእያንዳንዱ ማስታወቂያ ከአንድ ሺ ዩሮ በላይ ይከፈላታል፡፡
የስፖርት ግብዓቶች አቅራቢው ድርጅት Bigን ማስታወቂያ ትሰራለች፣ ቫንቩ በተሰኘ መተግበሪያ ላይ ፎቶግራፎቿን እያጋራች በርካታ ተከታዮችን ማፍራት ችላለች፡፡ በኢንስታግራም ወደ አራት ሚሊዮን የተጠጋ ተከታይ ያላት ሲሆን በየጊዜው የምትለቃቸው ፎቶግራፎቿ በብዙ ሺህ የሚቆጠር እይታና አስተያየቶችን አግኝተዋል፡፡
የሰው ሰራሽ አስተውህሎት ውጤት መሆኗን ያልተረዱ ዝነኛ ሰዎች ጭምር በውስጥ መስመር በርካታ መልዕክቶችን ይልኩላታል፡፡ አንድ ቀን ከአምስት ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት ያለው ስሙን ከመጥቀስ የተቆጠበ አንድ ዝነኛ የላቲን አሜሪካ ተዋናይ የእራት ግብዣ ጥያቄ አቅርቦላት ነበር ይላል ዲዛይነሯ ሩበን ክሩዝ፡፡ በገሃዱ አለም አለመኖሯን አላወቀም ነበር ባይ ነው ተዋናዩ፡፡
መጀመሪያ ሰሞን የኤጀንሲው ቡድን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከፎቶ ግራፍ ይልቅ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን እንደሚፈልጉና በብዛት እንደሚከተሉ ይታዘባል፡፡ በገሃዱ ዓለም ለሌለችው አይታና ለእዚህ መፍትሄ ያሉት ለተካታዮቿ የሚሰራጭ አንዳች ታሪክ መፍጠር ነበር፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የምትወድና ተግባቢ ማንነት ያላት ሆና ተቀረጸች፡፡ የአብዛኛው የማህበራዊ ትስስር ገጽ ተከታዮች ፍላጎት ሲጠና የአውሮፓውያኑ ባህል በብዛት በተጠቃሚው ዘንድ የሰረጸ ሆኖ ተገኘ፡፡ እናም አይታና የአውሮፓውያኑን ባህል እንድትይዝ ተደረገ፣ ጸጉሯም ሮዝ ቀለም እንዲይዝ ሆነ፡፡

በየሳምንቱ የኤጀንሲው ቡድን አይታናን በመጪዎቹ ሳምንታት የሚኖራትን እቅዶች ለማውጣት ይሰበሰባሉ፡፡ ምን እንደምታደርግ፣ የትኞቹን ቦታዎች እንደምትጎበኝ እና የትኞቹ ፎቶዎቿ በማህበራዊ ትስስር ገጸቿ ለተከታዮቿ እንደሚጋራ ይወስናሉ፡፡ የፎቶ ቀረጻ ብሎ ነገር የለም፣ የዲዛይን ባለሙያዎቹ በሰው ሰራሽ አስተውህሎት ታግዘው በፎቶ ቅንብር የአይታናን ውሎ ይሰራሉ፡፡
ለሰው ልጅ ሞዴሎች የምናወጣውን ከፍተኛ ክፍያ ቀንሶልናል፣ እንዲህ ስሩ እንዲያ ከሚል እስጥ አገባ ገላግሎናል ይላል ክሩዝ፡፡ ከአይታና በኋላ መሰል የሰው ሰራሽ አስተውህሎት ውጤት ፈላጊ የንግድ ተቋማት ተበራክተዋል፡፡ በአይታና ስኬትን የተቀዳጀው ክሉለስ ኤጀንሲ ማያ የተሰኘች ሌላ ዓይን አፋር ምዕናባዊ ሞዴል ፈጥረዋል፡፡
ኤጀንሲው የራሳቸውን ግላዊ ሞዴል በሚፈልጉ የንግድ ተቋማት ለእኛም ስራልን ጥያቄዎች እየጎረፉለት ነው፡፡ ለሰራተኛ የሚያወጡትን ክፍያ መቀነሱ ለመመረጡ አንዱ ምክንያት መሆኑ ተነግሯል፡፡ ትልልቅ የማስታወቂያ ክፍያዎችን መክፈል ለማይችሉ ድርጅቶች መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው ኤጀንሲው ይናገራል፡፡
በእዛው ልክ ወቀሳዎችም አላጡትም፡፡ ወጣቱ ትውልድ ከእነኚህ ምናባዊ ሞዴሎች ጋር ያልተገባ ፉክክር ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል የሚለው አንዱ ነው፡፡ የምዕናባዊ ሞዴሎቹ የተጋነነ ውበት ተከታዮቻቸውን ያልተፈለገ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደርጋል ሌላኛው ትችት ነው፡፡ ለስኬታማነት ወቅቱ የሚፈልገውን መከተል የግድ ይለናል የኤጀንሲው ምላሽ ነው፡፡

በስፋት አገልግሎት ላይ እየዋሉ የሚገኙት የሰው ሰራሽ አስተውህሎት ውጤቶች በብዙ መመዘኛዎች ተመራጭነታቸው እየጨመረ ነው፡፡ ለሰው ልጆችን ስራ እድል ማጥበብን ጨምሮ በርካታ ነቀፌታዎችም ይነሱባቸዋል፡፡
በየዕለቱ አይነቱንና ቅርጹን በመቀያየር ዓለምን እያስደመመ የሚገኘው የ ኤ አይ ቴክኖሎጂ ቀጣዩ የተጽዕኖ ስፍራ የሚያርፈው የፋሽን ኢንዱስትሪው እንደሚሆን እየተነገረ ነው፡፡ በየዕለቱ ሰውነታቸውን በአካላዊ ብቃት እንቅስቃሴና በተመጣጠነ ምግብ ቅርጻቸውን የሚንከባከቡ የዓለማችን ስመጥር ሞዴሎች ይህ ቴክኖሎጂ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል፡፡
ቀጣይ የሰው ሰራሽ አስተውህሎት ውጤት ምን ይሆን ? በምንስ ያስደምመን ይሁን? የሰርክ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል፡፡












