፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 03 2016| NBC ETHIOPIA- የምን ጊዜም ተወዳጅ እና ተናፋቂ የዓለማችን ምርጡ ተከታታይ ድራማ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማሙበታል። ከብዙዎች አእምሮ ሳይጠፋ እንደተወደደ ዓመታትን መዝለቅ ችሏል። ፕሪዝን ብሬክ
ፕሪዝን ብሬክ እ.ኤ.አ ከ2005 እስከ 2017 በ 5 ተከታታይ ምዕራፎች የቀረበ የአሜሪካ ተከታታይ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ ነው።የድራማው ታሪክ የሚያጠነጥነው ሊንከን ቡሮውስ እና ማይክል ስኮፊልድ የተባሉ ሁለት ወንድማማቾች የህይወት ታሪክ ላይ ነው።ሊንከን ቡሮውስ ባልፈጸመው ወንጀል ምክንያት የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ወደ ወህኒ ይወረወራል ። ማይክል ስኮፊልድም እቅድ በመንደፍ ወንድሙን ነጻ ለማውጣት ሲሞክር ያስመለክተናል።

ፕሪዝን ብሬክ የወንድማማችነት ትስስርን፣ ወንድማማቾቹ ከእስር ለመወጣት የሚያደርጉትን እልህ አስጨራሽ ጉዞ እና ያልተጠበቁ ሴራዎች በማስመልከት ልብ አንጠልጣይ በሆነ ትዕይንት ተመልካቾችን እያጓጓ የታየ ዘመን አይሽሬ ድራማ ነው።
የድራማው ዋና ገጸ-ባህሪያትም በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅ እና አይረሴ ሆነው አሁንም ድረስ ይታወሳሉ።ስለ ፕሪዝን ብሬክ ተወዳጅ ተከታታይ ድራማ ያስገርማሉ ያልናቸውን እውነታዎች በጥቂቱ ልናስመለክታችሁ ወደድን።
እ.ኤ.አ ከ2005 እስከ 2006 ባሉት ጊዜያት በመላው ካናዳ በመጀመሪያው ምዕራፍ ብቻ ከ18 እስከ 49 የእድሜ ክልል ባሉ 1.4 ሚሊዮን ተመልካቾች እንደታየ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በወቅቱ በሀገሪቱ ከነበሩ ከ20 የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎችም ቀዳሚውን ደረጃ ተቆናጦ ነበር፡፡
በአውስትራሊያ በእያንዳንዱ ምዕራፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የጥበብ አፍቃሪያን ተከታትለውታል፣ በፈረንሳይ እ.ኤ.አ ከነሃሴ 2006 ጀምሮ መታየት የጀመረው ፕሪዝን ብሬክ 5.5 ሚሊዮን ተመልካቾችን አግኝቷል፣ በመላው ዓለምም በበርካቶች በመታየት ከቀዳሚዎቹ መካከል መሆን ችሏል፡፡

ፕሪዝን ብሬክ ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ አጠቃላይ ከ 100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ፈሰሰ የተደረገበት ድንቅ ድራማም ነው።
በወቅቱ ፕሪዝን ብሬክ ተከታታይ ድራማ ሲተላለፍ የማይክል ስኮፊልድ ገጸ ባህሪይ የነበረው ከእስር የማምለጫ እቅድ በእውነተኛው ዓለም ላሉ ታሳሪዎች አነቃቂ ሊሆን ይችላል በሚል አሜሪካ ስጋት ገብቷት ነበር፡፡ በስጋትነት ከመመልከት ባሻገር በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 13 እስር ቤቶች ላይ እንዳይታይ እስከመከልከል ደርሳ ነበር፡፡
የፕሪዝን ብሬክ ተከታታይ ድራማ ገጽ ባህሪያት የሆኑት ሁለቱ ወንድማማቾች ለድራማው የተመረጡት ቀረጻ ለመጀመር ጥቂት ቀናት ሲቀሩት መሆኑ ብዙዎች ያሰገረመ ክስተት ነው።
የፊልሙ መለያ እስከመሆን የደረሰው የማይክል ስኮፊልድ ንቅሳት በጥንቃቄ የተነደፈ እና ትክክለኛ እንዲመስልም በርካታ ባለሙያዎች ተረባርበውበታል፡፡
የእስር ቤቱን እያንዳንዱን መውጫ መግቢያ የያዘው የማይክል ስኮፊልድ ንቅሳትም ጊዜያዊ በመሆኑ ቀረጻ በሚኖር ጊዜ ሁሉ እንደገና የሚሰራ ነበር። ይህም ድራማው ብዙ እንደተለፋበት አንዱ ማሳያ ስለመሆኑ ይነጋራል፡፡
የፕሪዝን ብሬክ ሌላኛው አስገራሚ እውነታ የፕሮዳክሽኑ ቡድን እውነተኛ የሆነ ስሜትን ለተመልካች ለማጋባት ድራማው የተሰራው በእውነተኛ ወይህኒ ቤት ሲሆን በአሜሪካ የወንጀል ታሪክ አደገኛ ነፍሰ ገዳይ በታሰረበት እና እ.ኤ.አ በ 2002 በተዘጋው ጆሌት ወይኒ ቤት ነው።

ፕሪዝን ብሬክ ተከታታይ ድራማ እ.ኤ.አ በ 2005 የፒፕል ቾይስ አዋርድን ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን መውሰድ ችሏል። በራሚን ድጃዋዲ የተቀናበረው የፕሪዝን ብሬክ ተከታታይ ድራማ ማጀቢያ ሙዚቃ እጅግ ተወዳጅነት ማትረፍ ያቻ ተወዳጅ ሙዚቃ ነው።
በ-ሃይማኖት ወርቁ












