፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 03 2016| NBC ETHIOPIA-ለብዙዎች ሞት ብሎም ለመሰረተ ልማት መውደም ምክንያት እየሆኑ ከሚገኙ የተፈጥሮ አደጋዎች መካከል የጎርፍ መጥለቅለቅ አንዱ ነው፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ከባድ መጠን ያለው ዝናብ በሚጥልበት ወቅት የሚከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ መፍትሔ የሌለው ተፈጥሮአው አደጋ ነው ፡፡
ይህ የተፈጥሮ አደጋ በሚሊየኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት ማለፍ መንስኤ ከመሆኑም በተጨማሪ ከተሞችን ወደ ፍርስራሽነት ሲለውጥም ይስተዋላል፡፡
ታሪክ በጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ከፍተኛ ጉዳትን አስከትለዋል ብሎ መዝግቦ ከያዛቸው አደጋዎች ውስጥ አንዱ በፈረንጆቹ 1931 በቻይና የተከሰተው አደጋ ተጠቃሽ ነው፡፡
አደጋው ለሶስት ቀናት ያህል የቆየ ሲሆን የአራት ሚሊየን ሰዎችን ህይወት አሳጥቷል አደጋውም እስከ አሁን ከተከሰቱት እጅግ አስከፊ የተፈጥሮ አደጋዎች ዋነኛው ያደርገዋል።
ይህ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ህይወታቸውን ከነጠቃቸው ሰዎች በተጨማሪ ይዞት የመጣው ጣጣ በዚህም አላበቃም እንደ ተቅማጥና ኮሌራ ያሉ ገዳይ የውሃ ወለድ በሽታዎች በፍጥነት እንዲስፋፉ አድርጓል፡፡በዚህም በሽታ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

በታሪክ በተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ ከጎበኛቸው ሀገራት መካከል የሆነችው ቻይና ከዚህ አደጋ በኋላም ቢሆን ከፍተኛ ጉዳትን ያስከተሉ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋዎች ገጥመዋታል በ1887 የደረሰባት አደጋም ሁለት ሚሊየን ዜጎቿን ህይወት የነጠቀ ነበር፡፡
በቅርቡ የወጣው የአየር ንብረት ለውጥ ሪፖርት እንዳመለከተው 700 ሚሊዮን ሰዎች ለዚህ አደጋ በጣም ተጋላጭ በሆኑ ስፍራዎች ህይወታቸውን ይመራሉ፡፡
የጎርፍ መጥለቅለቅ ከሚያስከፍለው የህይወት ዋጋ በተጨማሪ ለአፈር መሸርሸር መንስኤ እየሆነም ይገኛል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በሰው ልጆች ህይወትና ንብረት ላይ የሚያስከትለው ውድመት በዚህ ብቻ የሚገደብ አይደለም በዱር አራዊት ላይም የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ ቀላል እንዳልሆነ የሚወጡ የጥናት ውጤቶች አመላካች ናቸው፡፡
እንስሳቶቹ በአደጋው ከሚገጥማቸው የመስጠም አደጋ በተጨማሪ የበሽታ መስፋፋት ብሎም የመኖሪያ አካባቢያቸው መውደም ከሚደርስባቸው ጉዳቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የጎርፍ አደጋዎች እንደ ሄፓታይተስ ኤ እና ኮሌራ ያሉ የውሃ ወለድ በሽታዎችን የመስፋፋት እድልን ይጨምራሉ።
ታዲያ ለእነዚህና አይነት ችግሮች መንስኤ የሆነውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን በአደጋው ይበልጥ ተጠቂ የሆነችው ቻይና መፍትሔ ያለችውን ይዛ ብቅ ብላለች፡፡
በተደጋጋሚ በከተሞች የሚፈጠሩ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋዎችን ለመከላከል “ስፖንጅ ከተማ” የተሰኘ ጽንሰ ሀሳብ ሀገራት ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

“ስፖንጅ ከተማ” የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀው ቻይና ውስጥ ሲሆን ፕሮፌሰር ኮንግጂያን ዩ ጽንሰ-ሀሳቡን የፈለሰፈ ቻይናዊ የመሬት ገጽታ አርክቴክት ናቸው።
ይህ የስፖንጅ ከተማ ጽንሰ ሀሳብ የጎርፍ መጥለቅለቅ በሚከሰትበት ወቅት ውሃውን ለቀናት አቁሮ በመያዝ አደጋውን በመቀነስ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ የጎርፍ አደጋ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ከተሞች ውሃው በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲወጣ የሚያደርጉ የስፖንጅ ከተማ ጽንሰ ሀሳብን ተግባራዊ ማድግ እንዳለባቸው ተመራማሪዎች ይመክራሉ።
“የስፖንጅ ከተማዎች” የሚለው ቃል እንደ ዛፎች፣ ሀይቆችና መናፈሻዎችን የመሳሰሉ በርካታ የተፈጥሮ አካባቢዎችን ያማከለ ነው፡፡
እነዚህ አካባቢዎች ውሃን ይዞ በመቆየት ረገድ የራሳቸው የላቀ አቅም እንዳላቸው የሚታመን ሲሆን ይህንንም ሀሳብ ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩ የተለያዩ ሀገራት ይገኛሉ፡፡
ከእነዚህም መካከል ኒውዮርክ፣ለንደን፣ ሲንጋፖር፣ ሙምባይ፣ ኦክላንድ፣ ሻንጋይና ናይሮቢ ተጠቃሽ ናቸው።
አረንጓዴ የመሠረተ ልማት ቴክኖሎጂዎች በአፈር ውስጥ ለዝናብ ውሃ መምጠጥና ይበልጥ ዘልቆ እንዲገባ የሚያስችሉ በመሆናቸው ነው ለችግሩ መፍትሔ የተደረጉት፡፡
የስፖንጅ ከተማ አረንጓዴ መሠረተ ልማት የገጸ ምድር ውሃዎች ሰርጎ መግባት፣ መሳብ፣ ማከማቸትና ማፅዳትን የሚጠቃልል ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ መሰረተ ልማቶች በከተማው ውስጥ ከተገነቡት የመንገድ ስርዓትና ሕንፃዎች ጋር ሊጣመሩ እንደሚገባም ይነገራል፡፡












