፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 15 2016| NBC ETHIOPIA- የተወለደው በፈረንጆቹ የዘመን ቀመር ሐምሌ 30 ፣ 1947 በደቡባዊ ኦስትሪያ በግራዝ ከተማ አቅራቢያ ታል በተባለች መንደር ሲሆን፣ ገና በለጋ እድሜው ፣የሰውነት ግንባታ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ፊልሞች መመልከት፣ እግር ኳስ፣ ቦክስ እና ዋናን ጨምሮ በስፖርት ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ እንደነበረው ይነገርለታል።
የሆሊውድ መንደር ኮከቡ ኦስትሪያዊ እና አሜሪካዊ ተዋናይ፣ ነጋዴ፣ የቀድሞ ፖለቲከኛ እንዲሁም ፕሮፌሽናል ቦዲ ቢውልደር፣ አርኖልድ አሎይስ ሸዋርዜንገር።
ታዋቂው የሆሊውድ ተዋናይ ሸዋርዜንገር ክብደት ማንሳት ጀመረው ገና የ15 አመት ልጅ ሳለ ነበር ።
ከልጅነቱ ጀምሮ ቦዲ ቢውልደር መሆን ህልሙ እንደነበር የሚናገረው፣ ሸዋርዜንገር በአውሮፓ በበርካታ ውድድሮች ላይ በአካላዊ ብቃት እና በሰውነት ግንባታ ለመወዳደር ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው።
እ.ኤ.አ በ1968 በ21 አመቱ ወደ አሜሪካ በማቅናት የህይወቱን የሰኬት መንገድ ይጀምራል።በዚያኑም ዓመት ሸዋርዜንገር ሚስተር ዩኒቨርስን በመቀጠልም ሚስተር ኦሎምፒያ ለተከታታይ ሰባት ጊዜ በማሸነፍ ህልሙን እውን ማደረግ ቻለ ።

በሀገረ አሜሪካ ዝናን ለመቆናጠጥ ጊዜ ያልፈጀበት ሸዋርዜንገር በአስደናቂው የሰውነት ገጽታው ትኩረትን በመሳብ ወደ ፊልም ኢንዱስትሪ ጎራ እንዲል ጥያቄዎች ይቀርቡለት ጀመረ።
እ.ኤ.አ በ1970 የመጀመሪያውን ሄርኩለስ የተሰኘውን እና በአርተር አላን ሴይድልማን ዳይሬክት የተደረገውን የአሜሪካ አስቂኝ ፊልም ላይ በትወና መሳተፍ ቻለ። ይህም ለዛሬው የሸዋርዜንገር የትወና ስኬት በር የከፈተ ነበር፡፡
በመቀጠልም እ.ኤ.አ በ1977 በሰውነት ግንባታ ላይ ትኩረቱን አድርጎ በተሰራው ‹‹ፓምፒንግ አይረን›› በተሰኘው ዘጋቢ ፊልም ላይ በትወና ተሳተፈ። ከአመታት በኋላ በ1982 ኮናን ዘ ባርባሪያን በተሰኘ ልብ አንጠልጣይ እና በወቅቱ ተወዳጅነትን ባተረፈ ፊልም ላይ በመሪ ተዋናኝነት ተጫወተ፡፡ ፊልሙ በአካዳሚ ኦፍ ሳይንስ፣ ፊክሽን፣ ፋንተሲ ኤንድ ሆረር ፊልም ተሸላሚ መሆን የቻለ እና ለሸዋርዜንገር ሽልማት እና ዝናን ያስገኘለት ነበር፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላም የሳይንሳዊ ልብ ወለድ ዘውግ ባለው በጄምስ ካሜሮን ዳይሬክት የተደረገው ፣ የአሜሪካ ሳይንሳዊ ልብወለድ The Terminator1 እና Terminator 2 በተሰኙ ፊልሞች ብቃቱን አስመሰከረ፡፡ ፉልሙም ሮቦቶች በቅርብ ጊዜ ውስጥ አለምን እንደሚቆጣጠሩ ያስመለክታል።
ሸዋርዜንገርም የጎልደን ግሎብ ሽልማት፣የኒኬሎዶን Kids’ Choice Awards፣ የኤምቲቪ ፊልም ሽልማትን ጨምሮ በርካታ የተለያዩ ሽልማቶች በድንቅ ብቃቱ ማሸነፍ ችሏል።በ Best Male Performance በTerminator 2: እና Judgment Day የኤም ቲቪ አዋርድ አሸናፊ ሆኗል።
ከዚያም Judgment Day ፣ Commando፤ The Running Man , Predator, Total Recall እና , የተሰኙ ፊልሞችን ጨምሮ ከ40 በላይ ተወዳጅነት ባተረፉ ፊልሞች ላይ በትወና ተሳትፏል።
የዘርፈ ብዙ ሞያዎች ባለቤት ፣ ሸዋርዜንገር እ.ኤ.አ ከ1990 እስከ 1993፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እና የስፖርት ምክር ቤት ሊቀመንበር በመሆንም አገልግሏል። በኋላም በካሊፎርኒያ የአካል ብቃት እና ስፖርት ምክር ቤት በገዥው ፒት ዊልሰን ስር ሆኖ አገልግሏል። በስፖርቱ ዘርፍ ስሙ በጉልህ የሚነሳው ሸዋርዜንገር የባህል፣ የትምህርት እና የማህበረሰብ ማበልፀጊያ ፕሮግራሞችን ለወጣቶች የሚያቀርብ ICG የተባለ ፋውንዴሽንን መመስረት ችሏል፡፡ ፋውንዴሽኑ በሀገሪቱ በ15 ከተሞች የሚሰራ ሲሆን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ250ሺ በላይ ህጻናትን እና ከ400 በላይ በሆኑ ትምህርት ቤቶች ያገለግላል።

ሸዋርዜንገር በሰውነት ግንባታ በዓለም ታዋቂ ሆኖ ቆይቷል፤ በስፖርቱ ላይ በርካታ የሚባሉ መጽሃፎችን አበርክቷል፡፡ የምንጊዜም ታላቅ ቦዲ ቢውልደር በሚል ስሙን በጉልህ አኑሯል፡፡ በስፖርቱ ዓለም ትልቅ አበርክቶ ካሳረፉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አንዱም ሲሆን፣ ይህም የክብር አምባሳደርነትን እስከማግኘት አድርሶታል፡፡
ሸዋርዜንገር በፖለቲካ ተሳትፎውም የሚታወቅ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ2003 እስከ 2011 በካሊፎርኒያ በአስተዳደርነት አገልግሏል። የታይም መጸሄት እ.ኤ.አ ከ2004 እስከ 2007፤ 100 የአለም ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች ብሎ ካስቀመጠው ዝርዝር ሸዋርዜንገር አንዱ ነበር። ኑሮውን በካሊፎርኒያ ያደረገው የ75 አመቱ አርኖልድ ሸዋርዜንገር፣ አሁን ላይ እርጅና መጣው መጣው ቢለውም እጅ አልሰጥም በማለት የኔትፍሊክስ ቺፍ ኦፊሰር በመሆን ታታሪነቱን እያስመሰከረ ነው፡፡
በ- ሀይማኖት ወርቁ












