፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 15 2016| NBC ETHIOPIA- አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች በግብርና ፣ በህከምና ፣ እና በተለያዩ ዘርፎች የሰውን ልጅ ድካም በመቀነስ የላቀ አበርክቶ እንዳለ፤ቸው እሙን ነው፡፡
ድሮን ቴክኖሎጂ አሁን ላይ ለበርካታ አገልግሎቶች እየዋለ ይገኛል፡፡ በተለይ ደግሞ ሰው በማይደርስባቸው ቦታዎች በመሄድ እና ለአደጋ የተጋለጡ ስፍራዎችን በመድረስ ዘርፈ ብፉ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡
የአለም ሀገራትን እያሳሰበ ላለው የደን መመናመን ችግር ዘርን የሚዘራ የድሮን ቴክኖሎጂ በመፈጠሩ ለችግሩ ፈጣን ምላሽ እየሰጠ እንደሆነ አልጀዚራ የቴክኖሎጂ ጉዳዮቹን በሚዘግብበት አምዱ አስፍሯል፡፡
እያደገ የመጣው የደን መመናመን በአለም ዙሪያ የከፋ አደጋን እያስከተለ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ እና ለሙቀት መጨመር ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
የአለማችን ትልቁ ደን የሆነው አማዞን ባለፉት አስርት አመታት ውስጥ 20 በመቶው የሚሆነው ስፍራ መመናመኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ በርካታ ሀገራት በጀትን በጅተው እየሰሩ ይገኛሉ ፡፡

ከፍተኛ የደን መመናመን ካለባቸው ሀገራት አንዷ የሆነችው ብራዚል እ.ኤ.አ እስከ 2030 ድረስ 12 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን ለማልማት እና ስምንት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ይህንንም ደን መልሶ ማልማት ሂደትን ለማሳካት የድሮን ቴክኖሎጂን በዋናነት እየተጠቀመችም ትገኛለች፡፡
ባህላዊው ችግኝ ተከላ የሰው ሃይል ፣ ጊዜ እና ገንዘብን የሚጠይቅ ሲሆን በድሮን የሚደረገው የደን መልሶ ማልማት ግን ሰፊ ስፍራን በትንሽ ጊዜ ውስጥ ማዳረስ እንደተቻለ ነው የተገለጸው ፡፡
ድሮኖቹ ሰው ሊደርሰበት የማችሉ እና አደገኛ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ስፍራዎች ላይ ሳቀር ዘር እየዘሩም ይገኛሉ፡፡
አንድ ሰው አልባ ድሮኖን በደቂቃ 180 የዘር እንክብሎችን መበተን ይችላል ይህም የሰው እጅን በመጠቀም ከሚካሄደው ባህላዊ የደን መልሶ ማልማት 100 እጥፍ ፈጣን ነው ተብሏል።

ሰደድ እሳት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች በሰው የሚካሄድ የደን መልሶ ማልማት ለማስጀመር ቢያንስ ሁለት አመት የሚጠበቅ ሲሆን በድሮን ግን ሰደድ እሳቱ ከተከሰተ ከሁለት ወራት በኋላ ዘሩን ለማብቀል በቂ የሆነ ዝናብ ካለ የዘር መዝራት ሂደቱን መጀመር ይቻላልም ነው የተባለው፡፡
በብራዚል የምትገኘው ባሂአ እ.ኤ.አ በ2023 ከፍተኛ ሙቀት ያስተናገደች እና ዝናብም ሳታገኝ የቆየች ቢሆንም ምስጋና ለድሮን ቴክኖሎጂ ይግባና አሁን ላይ በመልሶ ማልማት ለውጥ እየታየ ነው እንደ አልጀዚራ ዘገባ፡፡
በድሮኖች ላይ የሚገጠም ካሜራ እና ሴንሰር በደን ውስጥ ያለውን የተጎዳ ስፍራ እና ያለውን የአፈር አይነት ለመለየት ያስችላል፡፡ ይህም ቦታው ላይ ያለውን ችግር ለይቶ አስፈላጊዉን እርምጃ ለመውሰድ እንደሚያስችል ይነገራል፡፡
በተጨማሪም በደን ውስጥ የሚረጩ የተለያዩ ፀረ ተባይ መድሃኒቶችን ለመርጨት ሌላው ስፍራ ሳይበከል የተፈለገውን ቦታ ብቻ ለማከም ድሮን ቀዳሚ ምርጫ እንደሆነም የዘርፉ ባለሞያወች ያስረዳሉ፡፡
እስካሁንም የደን መመናመንን ለመከላከል በአሜሪካ ፣ በብራዚል ፣ በአፍሪካ እና በአውሮፓ ሀገራት የድሮን ቴክኖሎጂ ጥቅም ለይ ውሏል፡፡
በ- የአብስራ ብርሀኑ












