፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሚያዚያ 24 2016| NBC ETHIOPIA- በዐቢይ ጾም የመጨረሻው ሳምንት ሰሞነ ሕማማት ካሉ ቀናት መካከል አራተኛው ዕለት ጸሎተ ሐሙስ ነው። በጸሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ትሕትና እና ፍቅር ዝቅ ብሎ የሐዋርያትን እግር ማጠቡ ለሰው ልጆች ትልቅ ትርጉም ያዘለ ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና እና ፍቅር እግራቸውን ዝቅ ብሎ ማጠቡ የሚያስተምረው ከሁሉ የበላይ የሆነ አምላክ፤ ዝቅ ብሎ በትሕትና ታናናሾቹን ማገልገሉን፣ የተቸገሩትን እንዲረዱ እንዲሁም እርስ በእርስ በመረዳዳት እንዲኖሩ ትምህርት የሰጠበት ነው።
ዕለቱ እንደ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ስርዓት መሠረት ጸሎተ ሐሙስ፣ ሕጽበተ እግር፣ የምሥጢር ቀን፣የሐዲስ ኪዳንና የነጻነት ሐሙስ ይባላል።
በስያሜዎቹ መሠረት ይህን ለማስታወስ ዛሬም ሊቃነ ጳጳሳትና ቀሳውስት ‹‹በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ፤ እኛም የአንተን አርአያነት ተከትለን የልጆቻችንን እግር እናጥባለን›› በማለት የምዕመናን እግር ያጥባሉ ትምህርተ ትሕትናን በተግባር ያስተምራሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ዕለቱ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ምሥጢረ ቁርባን ስለመመሥረቱና ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረቡ የሰው ልጅ ነጻነት ያገኘበት ነው ተብሎ ይታሰባል።
በጸሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ ካከናወናቸው ተግባራት በተጨማሪም በዕለቱ ትውፊታዊ ስርዓትን በጠበቀ ሁኔታ “ጉልባን” የተባለው ምግብ ይበላል።
ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚባላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብፅ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር፤ አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡
ያን ጊዜ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መብላት፤ ንፍሮ ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበርና ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓሉ ይታሰባል፡፡
በጸሎተ ሐሙስ ይህንን መሠረት በማድረግ የሚዘጋጀው ጉልባን አንዲሁም ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ይህም ጨው ውኃ የሚያስጠማ በመሆኑ የኢየሱስ ክርስቶስን መጠማት ያስታውሳል፡፡
ይህ ትውፊታዊ ሥርዓት ከእስራኤላውያን የመጣ ሲሆን በኢትዮጵያም አብዛኛዎቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ሥርዓቱ ዛሬም ይከበራል፡፡
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Website – https://nbcethiopia.com/news/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












