፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሚያዚያ 19 2016| NBC ETHIOPIA- አሁን ባለንበት በ 21ኛው ክፍለ ዘመን የሰው ልጆች አመጣጥ ተብለው ከሚታመኑት አንዱ የሆነው የዝግመተ ለውጥ ሂደት ወይንም The evolution theory እውን መሆኑን ማሳያ እንዲሁም በሰው ልጆች እና በጎሬላ መካከል የነበረውን የዝግመተ ለውጥ ሂደት እንደ ማረጋገጫ ተደርገው የሚቆጠሩ የቤተሰብ አባላት አሉ ቢባል ለሰሚውም ግራ የሚያጋባ ነው፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው በደቡብ ምስራቅ ቱርክ ራቅ ባለ የገጠራማ ስፍራ ለበርካታ አመታት እራሳቸውን ከማህበረሰቡ አግለው የሚኖሩ 19 የቤተሰብ አባላት አሉ፡፡
የኡላስ ቤተሰብ ተብለው የሚጠሩት የቤተሰብ አባላት 12ቱ እንደማንኛውም ሰው ጤነኛ የእድገት ስርአትን የተከተሉ ሲሆኑ፣ አምስት ሴቶች እና በህልፈት የተለያቸውን ጨምሮ 2 ወንድ የቤተሰቡ አባላት እድሜያቸውን ሙሉ በመዳፎቻቸው እና በእግሮቻቸው እንደ እንስሳት እየዳሁ መሄድን ተገደዋል፡፡
ወላጅ እናታቸው በልጅነታቸው እንደማንኛውም ህጻን ይድሁ እንደነበር እና ከፍ ሲሉ ቆሞ ከመራመድ ይልቅ በመዳፎቻቸው እና በእግራቸው መራመድ መጀመራቸውን ትናገራለች፡፡

‹‹እስከ 9 ወራቸው ድረስ እንደማንኛውም ህጻን እንዲህ ነበር የሚድሁት፤ ከፍ እያሉ ሲመጡ ግን ቀና ማለት ከነሱ እራቀ ሙሉ ለሙሉ በእጅ እና በመዳፋቸው መሄድ ጀመሩ››፡፡
ከ 18 እስከ 34 አመት እድሜ የሚገኙት የኡላስ ቤተሰብ አባላት የልጅነት ጊዜያቸውን በደስታ ማሳለፍ አልታደሉም፡፡ ላለፉት በርካታ አመታት ከማህበረሰቡ ተገለው እና ተደብቀው ነው የኖሩት፤ ቤተሰቦቻቸው እነርሱን ለማሳደግ ብዙ ፈተናዎችን እንዳሳለፉም ይናገራሉ፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ስለኡላስ የቤተሰብ አባላት የተሰማው፣ የቱርክ ሳይንሳዊ የጥናት መፅሄቶች ባስነበቡት ጽሁፍ ነበር፤ ይህንን ተከትሎ ቢቢሲ ቴሌቪዥን ወደ ወደቤተሰቦቹ መኖሪያ መንደር በማቅናት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2005 The family that walk on all four የተሰኘ ዶክመንተሪ አሰናድቶ ቤተሰቡን ለዓለም አስተዋውቋል፡፡
የኢቮሊውሽነሪ ሳይኮሎጂስት ባለሞያው ፕሮፌሰር ኒክ ሀምፍሬይ እንደዚ አይነት ሁነት በህይወታቸው አጋጥሟቸው እንደማያውቅ እና በቱርክ የጤና መፅሄቶች ላይ ታሪኩን ለመጀመሪያ ጊዜ ካነበቡበት ወዲህ ስለቤተሰቡ ለማወቅ ጉጉት እንዳደረባቸው ይናገራሉ፡፡
የኡላስ ቤተሰብ ለዓመታት እራሳቸውን አግልለው በገጠራማ መንደር መኖራቸው እና ወላጆቻቸው ቢሆኑ እድሜያቸው የገፉ መሆኑ ፣ ጠንከር ያለ ህክምና እንዳያገኙ እንዲሁም ከሌሎች ሰዎችም መራመድ የሚያግዛቸው መደገፊያዎችን እንዳያገኙ አድርጓቸዋል፡፡

ሳይንቲስቶች የኡላስ ቤተሰብ አባላት ጉዳይ ከሰሙበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ምርምሮችን አድርገዋል፡፡ ይሁንና የቤተሰቡን አካላዊ አፈጣጠር ወሰብሰብ ያለ በመሆኑ ይህ ነው የሚል መላምት ላይ ለመድረስ መስጠት አዳጋች እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡ አጥንቶቻቸው ከሰው ልጆች የአጥንት አወቃቀር የተለየ እና ያልተለመደ እንደሆነ በእንግሊዝ ሊቨርፑል ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑ ሳይንቲስቶች ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ሴረብለም በተባለው የአዕምሮ ክፍላቸው ላይ ከተፈጠረ ችግር ጋር ተያይዞ የተከሰተ ሊሆን ይችላል በሚል ግምት ምርመራ ቢደረግም አዲስ ውጤት ማግኘት አልተቻለም፡፡
በምርመራ ሂደቱ እና እየተደረገላቸው ባለው ክትትል አብዝኞቹ ደስተኛነታቸውን ቢገልጹም፣ ሁሴን የተባለው የቤተሰቡ አባል ግን ጊዜው እንደረፈደ እና ምንም አይነት ለውጥ እንደማይመጣ በቁጣው ይገልጻል፡፡
ከኡላስ ቤተሰብ አባላት አፈጣጠር ጀርባ ያለው ሚስጥራዊ እና ግርምትን ጫሪ ሁኔትን በተመለከተ የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች ዛሬም መደምደሚያ ባያገኙም እስካሁን የተሄደባቸው ርቀቶች በትንሹም ቢሆን ለቤተሰቡ እረፍት የሰጠ ይመስላል፡፡
በ-የአብስራሚሊዮን












