፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሚያዚያ 21 2016| NBC ETHIOPIA- ገጣሚ፣ ተወዛዋዥ፣ ዘፋኝ፣ አክቲቪስት ብሎም ምሁር ማያ አንጀሉ በዓለም ታዋቂ ደራሲ ነበረች።
በይበልጥ የምትታወቀው በልዩና ፈር ቀዳጅ ግለ-ታሪካዊ የአጻጻፍ ስልቷ ነው።
በአውሮፓውያኖቹ ኤፕሪል 4, 1928 ፣ በዓለም ላይ ማያ አንጀሉ በመባል የምትታወቀው ማርጌሪት አን ጆንሰን በአሜሪካ ተወለደች።
በወላጆቿ በተፈጠረው ፍቺ ምክንያት፣ አንጀሉ ገና በለጋ እድሜዋ ከአያቷ ጋር ለማደግ ተገደደች።
ታላቅ ወንድሟ ቤይሊ ለአንጀሉ “ማያ” የሚል ቅጽል ስም አወጣላት።በሰባት ዓመቷ ለአጭር ጊዜ ወደ እናቷ እንክብካቤ ስትመለስ አንጀሉ በእናቷ የወንድ ጓደኛ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተፈጸመባት፡፡
በኋላ ታስሮ ከአመታት በኋላ ከእስር ቢፈታም ተገድሏል፡፡በግለሰቡ ሞት ውስጥ በደረሰባት ጉዳት እጇ እንዳለበት በማመን አንጀሉ ለስድስት ዓመታት ያህል ምንም አይነት መናገር ተስኗት ቆይታለች፡፡
በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆናም ከሄደችበት የእናቷ መኖሪያ በመመለስ እንደገና በአርካንሳስ ከአያቷ ጋር መኖሯን ቀጠለች፡፡ አንጀሉ ለጽሑፍ ና ለእንግሊዘኛ ቋንቋ የነበራት ፍላጎት ገና ከልጅነቷ ጀምሮ ይታይ እንደነበር የሚያውቋት ሰዎች ይመሰክሩላታል።

በልጅነቷ ውስጥ፣ ከድርሰቶችን በተጨማሪም ግጥሞችን ትጽፋለች፣ ወደ አርካንሳስ ስትመለስ ግጥም ፍላጎት ነበራትና የሼክስፒር ስራዎችን በቃሏ ሸምድዳ ለመያዝም ችላ ነበር፡፡
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ በፊት አንጀሉ በዚህ ጊዜ በኦክላንድ ፣ ካሊፎርኒያ ትኖር ወደ ነበረችው እናቷ ተመለሰች።
በጆርጅ ዋሽንግተን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብታ በካሊፎርኒያ የሰራተኛ ትምህርት ቤት የዳንስና የድራማ ኮርሶችን ወሰደች።
ጦርነቱ ሲቀሰቀስም አንጀሉ የሴቶች ጦር ሰራዊት አባል ለመሆን አመለከተች።
ይሁን እንጂ የኮሚኒስት ግንኙነት አለው በተባለው የካሊፎርኒያ የሰራተኛ ትምህርት ቤት ውስጥ በመሳተፍ ማመልከቻዋ ውድቅ ተደረገ።
ገና የ15 ዓመት ታዳጊ የነበረች ብትሆንም ሥራ ለመቀጠር ቆርጣ ተነስታ ለጎዳና ተቆጣጣሪነት ለማመልከት ወሰነች።
ይሁን እንጂ አንጀሉ በቀለሟ ምክንያት መጀመሪያ ላይ ማመልከቻ እንዳታቀርብ ተከልክላ ነበር።
እሷ ግን ተስፋ ሳትቆርጥ ለሶስት ሳምንታት በየቀኑ ለስራ ማመልከት እንዲፈቀድላት ጠይቃለች፡፡
ሆኖም ጥያቄዎቿ ሁሉ ውድቅ የተደረገባት ሲሆን በመጨረሻም ኩባንያው ተጸጽቶ ማመልከቻ ሰጣት። ከህጋዊ የስራ እድሜ በታች ስለነበረች 19 አመትዋ እንደነበረች ጻፈችና ለቦታው ተቀባይነት በማግኘቷ በሳን ፍራንሲስኮ የመንገድ መኪና መሪ ሆና የሰራች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ አሜሪካዊ ሴት ሆነች።

አንጀሉ ለአንድ ሴሚስተር ተቀጥራ ከሰራች በኋላ ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ ወሰነች።
በ1944 ክረምት ከሚሽን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቃ ብዙም ሳትቆይ የመጀመሪያ ልጇን ክላይድ ቤይሊ ጆንሰን የተሰኘውን ልጅ ወለደች።
ከተመረቀች በኋላ፣ አንጀሉ እራሷንና ልጇን ለመርዳት ተከታታይ የሆኑ ያልተለመዱ ስራዎችን ለመስራት ተገደደች፡፡
በአውሮፓውያኖቹ 1949 በአሜሪካ የባህር ኃይል ውስጥ የኤሌክትሪክ ሠራተኛ የሆነውን ቶሽ አንጀሎስ ጋር ትዳር ብትመሰርትም ከሶስት አመት በላይ መሻገር ሳይችል ቀርቶ በ1952 በፍቺ ተጠናቀቀ፡፡
አንጀሉ በሙዚቃ እንዲሁም ውዝዋዜ ባላት ችሎታ በተለይም በካሊፕሶና በካባሬት ስታይል ትታወቃለች።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1950 ዎቹ ውስጥ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ብሎም በሰሜን አፍሪካ ከፍተኛ የአልበም ሽያጭ አግኝታለች፡፡
በ1950 በኒውዮርክ ከተማ የሚገኙ አፍሪካ አሜሪካዊ ጸሃፊዎች የጥቁር ደራሲያንን ህትመት ለመንከባከብና ለመደገፍ የሃርለም ጸሐፊዎች የተሰኘ ማህበርን አቋቋሙ።

አንጀሉም ይህንን ማህበር በ1959 የተቀላቀለች ሲሆን በሲቪል መብቶች ንቅናቄ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ችላለችና የደቡባዊ ክርስቲያናዊ አመራር ኮንፈረንስ ሰሜናዊ አስተባባሪ ሆና ለመሾምም በቅታለች፡፡
በ1969፣ አንጀሉ የልጅነት ህይወቷ እና የህይወት ታሪኳ ላይ ያተኮረ መጽሀፍ ማሳተም ቻለች፡፡
በልጅነቷ በደረሰባት ጉዳትና ዘረኝነትን ለመቋቋም የነበራትን ጥንካሬ ባሳተመችው መጽሀፍ በማስተጋባት ለብሔራዊ መጽሐፍ ሽልማት እጩ መሆን ቻለች፡፡
በወቅቱ ቀላል የማይባሉ ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ምክንያቶች መጽሐፉን ለማገድ ጥረት ሲያደርጉ የነበረ እንደሆነ የግል ታሪኳ ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
መጽሀፉ በአለም ዙሪያ ከአንድ ሚሊየን በላይ ቅጂዎች የተሸጡ ሲሆን በብዙ ቋንቋዎች ተተርጉሞም ለተደራሲያን ማድረስ ችላ ነበር፡፡
ብዙ የግጥም ጥራዞችን ከመጻፍም በተጨማሪ በተለያዩ አለም አቀፍ የመሪዎች ጉባኤ ላይ በመገኘትም ስራዎቿን ማቅረብ ችላለች፡፡ከዚህም ባሻገር በ1995 የግራሚ አዋርድ አሸናፊ ሆናለች፡፡
ለሥነ ጽሑፍ ዘርፉ ባበረከተችው አስተዋጽኦ በአሜሪካ ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በብዙ ድርጅቶች ዘንድ እውቅና አግኝታለች።
በ1981 ዋክ ፎረስት ዩኒቨርሲቲ ለአንጀሉ ሬይናልድስ የአሜሪካ ጥናት የፕሮፌሰርነት ማዕረግን ሰጥቷታል፡፡












