አዲስ አበባ | ሚያዚያ 01፣ 2016| NBC ETHIOPIA-የጸሃይ ግርዶሽ ዓለም ከምታስተናግዳቸው አስደናቂ የተፈጥሮ ክስተቶች መካከል አንዱ ነው። የፀሐይ ግርዶሽ ተከሰተ የሚባለው የተወሰነው የመሬት ክፍል በጨረቃ ጥላ ስር ሲወድቅ ነው።
የጸሀይ ግርዶሽ ጨረቃ በፀሀይና በመሬት መካከል ስታልፍ የጨረቃ ጥላ ፀሃይ ላይ አርፎ ፀሀይን እንዳናይ የሚያደርገን ድንቅ የተፈጥሮ ክስተት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በተወሰኑ የአለማችን ክፍሎች ላይ የቀን ጨለማን ይፈጥራል።
በአስርት አመታት መካከል የሚከሰተውን አስደናቂ የተፈጥሮ ክስተት የጸሀይ ግርዶሽን ለማየትም ሚሊዮኖች በጉጉት ይጠባበቃሉ።
ታዲያ ከሰሞኑም በዛሬው እለት በከፊል እና ሙሉ በሙሉ በበርካታ የአለም ሀገራት ላይ የጸሀይ ግርዶሽ እንደሚከሰት ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡት መቆየታቸው ይታወሳል።

የስነ-ፈለክ ተመራማሪዎች መላምታቸውን ያረጋገጠው ይህ ክስተት ብዙዎችን አስደንቋል፡፡
በሰሜን አሜሪካ የተከሰተው የፀሐይ ግርዶሽ ከሰባት ዓመታት በኃላ ዳግም ተከስቷል፡፡
ይህ የፀሐይ ግርዶሽ ለቀጣይ 20 አመታት ዳግም አይከሰትም የሚሉት የስነ-ፈለክ ተመራማሪዎቹ በትላንትናው እለት የተከሰተው የጸሀይ ግርዶሽ እ.ኤ.አ. በ2017 በአሜሪካ የባህር ዳርቻ ከተከሰተው አጠቃላይ የፀሐይ ግርዶሽ እጥፍ ያህል የረዘመ ነው ብለዋል፡፡
አጠቃላይ የፀሀይ ግርዶሹም 115 ማይል ስፋት ያለው ሲሆን በሜክሲኮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ካናዳን ያጠቃለለ ስለመሆኑ በርካታ አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በቀጥታ ስርጭት ሲዘግቡ ቆይተዋል፡፡
የጸሃይ ግርዶሹ በስፋት ከተስተዋለባቸው አገራት መካከል ዩናይት ስቴትስ ቀዳሚዋ ስትሆን በአገሪቷ በ13 ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ በመቶዎች በሚቆጠሩ ከተሞች ተስተውሏል፡፡
የጸሀይ ግርዶሹ በተለያዩ አገራት ከ 3 ደቂቃ እስከ አራት ደቂቃ ድረስ እርዝማኔ እንደነበረው ተመላክቷል፡፡
ይህንን አስደናቂ የጸሀይ ግርዶሽ ለማየት በሚሊዮን የሚጠጉ አሜሪካውያን እንዲሁም ተጨማሪ አለም አቀፍ ጎብኝዎች በክስተቱ ቦታ ታድመዋል፡፡
የፀሀይ ግርዶሹ የሚከሰትበት ትክክለኛ ጊዜ እንደየግዛቱ እና እንደየ ሰዓቱ ይለያያል ይላሉ የስነ-ፈለክ ተመራማሪዎቹ ። የግርዶሹ መታየትም የአየር ጸባይ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ይሆናል።

በዚህም ሳቢያ የዩናይትድ ስቴትስ አብዛኞቹ ግዛቶች እያስተናገዱት ባለው የአየር ጸባይ ሁኔታ ሳቢያ በትላንትናው እለት የተስተናገደው የጸሃይ ግርዶሽ ሊያመልጣቸው እንደሚችል የብሔራዊ የአየር ሁኔታ አገልግሎት መላምቱን አስቀምጧል፡፡
በትላንትናው እለት የተከሰተው ግርዶሹ ከሜክሲኮ ፓሲፊክ የባህር ዳርቻ የጀመረ ሲሆን ከዚያም ከቴክሳስ ግዛት ወደ ሌሎች ሊዳርስ ችሏል፡፡
“ክስተቱ እንደ አለም መጨረሻ ይመስላል፤ ቀደም ሲል በእስያ፣ በአውስትራሊያ፣ በሰሜን እና በደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በአፍሪካ በመዘዋወር የፀሐይ ግርዶሹን ማየት ችያለው ሲል በሜክሲኮ የጸሀይ ግርዶሹን ለማየት የተገኘው ሪያን ሚሊጋን እንዲህ ሲል ክስተቱን ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡
ሚሊጋን ለራሱ ‘ግርዶሽ አሳዳጅ’ የሚል ቅጥያ ስያሜን ሰጥቷል። ሜክሲኮ ውስጥ ክስተቱን ሲመለከት ለ12ኛ ጊዜ መሆንም ተናግሯል።ክስተቱም እጅግ ደስ የሚል እና አዲስ ልምድ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
የፀሐይ ግርዶሹን በመሣሪያ ታግዞ ካልሆነ በስተቀር በዓይን በቀጥታ ለማየት መሞከር ጉዳት እንደሚያስከትል የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
እድል ቀንቷቸው ሙሉ ግርዶሹ በሚከሰትበት ስፍራ የነበሩ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ሰዎች አይናቸውን ከጉዳት ለመከላከልም መነጽር ተጠቅመው ሁነቱን በቀጥታ ሊከታተሉ ችለዋል፡፡

በስንት ጊዜ አንዴ የሚከሰተውን ሁነት መታደም ላልቻሉ የአሜሪካው የጠፈር ምርመር ኤጀንሲ ናሳ ግርዶሹ ከሚከሰትባቸው ስፍራዎች በቀጥታ ስርጭት ለበርካታ ሰአታት ሲያስተላልፍ ቆይቷል፡፡
ይህንን የተፈጥሮ ክስተት ለመመልከት ወደ ቦታው ያቀናው አንድ አሜሪካዊ ከሁነቱ በፊት እንዲህ ሲል የተሰማውን ስሜት ይገልጻል።
ይህንን አስደናቂ ክስተት ለመመልከት ለሁለት ሰአት ከግማሽ የሚሆን መንግድ ተጉዢ ነው እዚህ የደረስኩት እናም ከዚህ የበለጠ ግልጽ ሆኖ የሚታይበት ሌላ ቦታ ካለ እራሱ 9 ሰአትም ቢሆን መኪናዬን አሽከርክሪ ለመሄድ ፈቃደኛ ነኝ ። በተቻለ መጠን በደንበ ማየት እፈልጋለሁ። ክስተቱን ሳስብ ገና ደስ የሚል ስሜት ይፈጥርብኛል አስደናቂ ነው፡፡
ቀጣዩ የፀሐይ ግርዶሽ እ.ኤ.አ. በነሐሴ 12 2026 የሚከሰት ሲሆን በስፔን፣ በአይስላንድ እና በግሪንላንድ ላይ ያልፋል ተብሏል።
አስደናቂ የተፈጥሮ ክስተት የሆነው የጸሃይ ግርዶች በአለማችን በተለያዩ አገራት በተለያዩ ወቅቶች የሚከሰት ሲሆን ኢትዮጵያም በሰኔ 14 2012 በተለያዩ አካባቢዎች የፀሐይ ግርዶሽን ማስተናገዷ ይታወሳል፡፡
በ-ሀይማኖት ወርቁ












