አዲስ አበባ | መጋቢት 16፣ 2016| NBC ETHIOPIA -በዘመናችን ሰዎች በተለያዩ የጤና እክሎች ሲገጥሟቸው ሊያግዛቸው የሚችል ህክምና ያገኛሉ፡፡ ህክምና መፍትሄ መስጠት ሳይችል ሲቀር ደግሞ ቀሪ እድሜያቸውን በቴክኖሎጂ በመታገዝ የተለያዩ መሳሪያዎችን በመጠቀም ሲቀጥሉ ይስተዋላል፡፡
የመተንፈሻ አካላት ችግር ላለባቸው ሰዎች ተብለው የሚሰሩ ማሽኖች ደግሞ ቁጥራቸው በርከት ያለ ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ iron lung ወይም የብረት ሳምባ አንዱ ነው፡፡ የመተንፈሻ ጡንቻዎችን መቆጣጠር ያቃታቸውን ታማሚዎች አተነፋፈስ ለማስተካከል የተሰራ ትልቅ አግድም ሲሊንደር መሰል መሳሪያ ነው፡፡ ይህ የብረት ሳንባ መሳሪያ ከፍተኛ እንክብካቤ በማድረግ ለብዙዎች በህይወት መቆየት መፍትሄ የሰጠ ነው፡፡

መሳሪያው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከከባድ የሳንባና የፖሊዮ ህመም ጋር እንዲኖሩ አስችሏል፡፡ ከባድ የሳንባና መሰል የቫይረስ ኢንፌክሽን ሰውነትን በፍጥነት የሚያጠቃ ሲሆን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የመተንፈሻ ጡንቻዎች በማዳከም ወደ ሽባነት ሲያልፍም ለሞት ሊዳርግ ይችላል፡፡
ነገር ግን ይህን የብረት ሳንባ ህመምተኞች አየር እንዲያገኙ በማድረግ የተጎዳውን ሳንባ እንዲሰራና የግለሰቡ ህይወት ለዓመታት እንዲቀጥል ለማድረግ ያስችላል፡፡
ይህ የብረት ሳንባ የህጻናትን ህይወት ለመታደግ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው እ.ኤ.አ. በ1928 እንደሆነ ታሪክ ያስረዳና፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የፖሊዮ ወረርሽኝ በአለም ዙሪያ በተበከለ ምግብ እና ውሃ ተሰራጭቶ ነበር፡፡ እናም ከክትባት ባለፈ የብረት ሳንባ ከባድ ጉዳት ለደረሰባቸው ዋናው የሕክምና ዘዴ ሆኖ በማገልገል ለህክምናው ዘርፍ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አሳይቷል፡፡
መሳሪያው በዋነኛነት የአየር ማናፈስ ስራን እንደሚሰራ ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት፡፡ አየር ወደ ታካሚ ሳንባ ውስጥ በግፊት እንዲገባ በማድረግ ሳንባው ስራውን እንዲሰራ ያግዛል፡፡
ይህ ማሽን ሲነስ በአለም አቀፍ ደረጃ ስሙ የሚነሳው በቅርቡ ህይወቱን ያጣው ፖል አሌክሳንደር ነው፡፡ ፖል 70 አመታት ባሳየው ትዕግስትና እና ፅናት በአለም ዙሪያ ስሙ የገነነ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ፖል አሌክሳንደር በፖሊዮ ከተያዘ ከ70 ዓመታት በላይ በብረት ሳንባ ውስጥ ኖሯል። በብዙዎች በማህበራዊ ሚዲያ ፖሊዮ ፖል ተብሎ የሚጠራው ይህ ግለሰብ በ78 አመቱ ዳላስ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡
ታዲያ ዛሬ ምስጋና ለቴክኖሎጂ ይሁንና የቀደመው የብራት ሳምባ ወደ ዘመናዊ ICU ወይንም የፅኑ ህሙማን ክፍል ለመቀየር ችሏል፡፡ICU በፅኑ ለታመሙ ሰዎች ሕክምና እና ክትትል የሚሰጡ ልዩ የሆስፒታል ክፍሎች ናቸው። በልዩ የሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች የታቀፉ እና የተራቀቁ የክትትል መሳሪያዎችን ይይዛል፡፡ በተጨማሪም የትኛውን የአካል ክፍል ስራ ተክተው መስራት የሚችሉ በርካታ መሳሪያዎች በዚሁ ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ቴክኖሎጂው የብረት ሳምባውን የመተንፈሻ አካል ድጋፍ መሰረት በማድረግ ለዘመናዊ የፅኑ ህሙማን ክፍሎች (ICU) እድገት ትልቅ ሚና መጫወቱን ቢቢሲ በዘገባው አትቷል፡፡ የብረት ሳምባው የተነደፈው ከጭንቅላት በስተቀር የታካሚውን አጠቃላይ አካል የሚሸፍን ባለመሆኑ አጠቃለይ የሰውነት ክፍልን ለመቆጣጠር እንዲያመች ተደርጎ አይሲዩ መሰራቱ ተጠቁሟል፡፡
በእርግጥ የብረት ሳምባው የመተንፈሻ አካልን ሽባ የሆኑ ታካሚዎች እንዲ ያድኑ በማድረግ የረጅም ጊዜ የመተንፈሻ አካላት ድጋፍ በመስጠት ውጤታማ መሆኑን ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ ይህም ለመተንፈሻ አካላት ድጋፍ መስጠትና እና ዘመናዊ አይሲዩዎችን መመስረት መንገዱን ከፍቷል ነው የተባለው፡፡

ተመራማሪዎች እና የሕክምና ባለሙያዎች በብረት ሳምባው መርሆች ላይ በመደገፍ በአይሲዩ የአየር ማናፈሻ ዘዴዎችን በመመርመር ኦክሲጅንን ወደ ሳንባ የማድረስ ሂደት ሁለገብ እና ቀልጣፋ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ የብረት ሳምባዎች በአብዛኛው በዘመናዊ የአየር ማራገቢያ መሳሪያዎች እና በ(ICU) ውስጥ በሚገኙ ሌሎች የላቁ መሳሪያዎች ተተክተዋል፡፡
አይሲዩ ከመተንፈሻ አካል ባሻገር የበርካታ የአካል ክፍሎችን ስርዓትን ለመቆጣጠር የሚያግዝ መሳሪያ ነው፡፡ በዋናነት ልዩ እንክብካቤ እና ክትትል የሚሹ በጠና የታመሙ ታካሚዎችን ጤና ለማረጋጋት እና ለማሻሻል የሚያግዝ ዘመናዊ ክፍል መሆኑንም ቢቢሲ በዘገባው አካቷል፡፡
ለፅኑ ሕመምተኞች ልዩ እንክብካቤ ስለሚሰጡ የአይሲዩዎች መመስረት በጤና እንክብካቤ ውስጥ ትልቅ እድገት ሆኗል ተብሏል፡፡ አይሲዩ የላቁ የህክምና መሳሪያዎች፣ ከፍተኛ የሰለጠኑ የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች እና ሁለገብ የሆነ ክትትል፣ ድጋፍ እና ህክምና ስለሚደረግበት አስፈላጊነቱ ወሳኝ መሆኑን ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡












