አዲስ አበባ | መጋቢት 06፣ 2016| NBC ETHIOPIA -በርካታ የአማኝ ቁጥር ያላቸው ሁለቱ ሃይማኖቶች እስልምና እና ክርስትና የጾም ወቅት ላይ ይገኛሉ፡
የሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖት ተከታዮች የጾም ወቅቱን የተለያዩ ሀይማኖታዊ ተግባራትን በመፈጸም በጸሎትና ተመስጦ ከፈጣሪያቸው ይገናኛሉ፡፡
እነዚህ ሀይማኖቶች ተከታዮቻቸው በመከባበርና በመተሳሰብ እንዲኖሩ ሲሰብኩና ሲያስተምሩ ዘመናትን ተሻግረዋል፡፡
ከአመታት በፊት ከወደ አሜሪካ የተሰማው መረጃ በሁለቱ እምነት ተከታዮች መካከል ያለውን ቅርበትና መተሳሰብ የሚያሳይ ነው ተብሎለታል፡፡
ነገሩ ወዲህ ነው በአሜሪካዋ ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አምልኮ የሚፈጽሙት የክርስትና እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ የእስልምና እምነት ተከታዮችም ጭምር ናቸው፡፡
ኢፒፋኒ ተብሎ በሚጠራው በዚህ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚሰማው ቅዳሴ ብቻ ሳይሆን አዛንም ጭምር ነው፡፡
በመቶዎች የሚቆጠሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች በየሳምንቱ አርብ አርብ የሰላት ስነ-ስርዓታቸውን ለመፈጸም ወደዚህ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ያመራሉ፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች የጸብና የጭቅጭቅ መንስኤ የሆነው የእምነት ጉዳይ በዚህ ስፍራ ግን የመተሳሰብ ማሳያ ተደርጎ ይቀርባል፡፡
የኢፒፋኒ ቤተክርስቲያን የተመሰረተው እንደ አውሮፓውያኖቹ አቆጣጠር በ1887 ነው፡፡በዚህ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ግድግዳ ላይ የተለያዩ ሀይማኖታዊ ምስሎች የሚታዩ ሲሆን በየሳምንቱ አርብ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሰላት ስነ- ስርዓታቸውን ይከውኑበታል፡፡
ፋሩቅ ሰኢድ ከስምንት አመት በፊት የመስገጃ ስፍራ ለሚያስፈልጋቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች ቤተ ክርስቲያኒቷ በሯን ከከፈተችበት ጊዜ ጀምሮ ለጁምዓ ሶላት ሲታደም ቆይቷል፡፡ፋሩቅ በዚህ ስፍራ የጁምዓ ሰላት ሲጀመር 50 ሰዎች ብቻ እንደነበሩ ይናገራል፡፡
ቄስ ኤልዛቤት ጋርድነር ይህ የቤተ ክርስታኒቷ ተግባር ለሰላምና መዋደድ ሲባል የተከወነ መሆኑን አጽናኦት ሰጥተው በአለም ላይ የሰላም እጅና እግሮች ልንሆን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሌላው በዚህ ስፍራ ለጁምዓ ሰላት ወደዚህ ቤተ ክርስቲያን የሚመጣው ሰኢድ ቦንድ ወደ እስልምና እምነት የገባው በወጣትነቱ ነበር፡፡
የራሴ የሚለው መኖሪያ ቤት የሌለው ሰኢድ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሆዴን ብቻ ሳይሆን ነፍሴንም መግባዋለች ሲል ይናገራል፡፡
የሀምሳ አመት ጎልማሳው ሰኢድ ቦንድ ከሶስት አመት በፊት ጀምሮ በዚህ ስፍራ የጁምዓ ሰላትን ሲከውን የቆየ ሲሆን የጁምዓ ሰላትን ለሚሰግዱ አማኞች ስፍራውን ከሚያሰናዱ ቤት አልባ ሰዎች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡
የአምልኮ ስፍራው ከአመታት በፊት በ50 ሰዎች ብቻ የሰላት ስነ ስርዓት ይከወንበት እንጂ አሁን ላይ ትልቁ የሙስሊሞች ጉባዔ እንደሆነ ፋሩቅ ተናግሯል፡፡
ሁሉም የሰው ልጅ የሃይማኖት ድንበር ሳይገድበው እርስ በእርሱ ሊተጋገዝና ሊተባበር ይገባዋል የሚለው ፋሩቅ የኢፒፊንያ ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ትልቅ ማሳያ ናት ብሏል፡፡
የእስልምና እምነት መምህራን የክርስትና እምነት ተከታዮች በነብዩ ሙሃመድ መስጅድ ውስጥ አምልኮ መፈጸማቸውን ያስተምራሉ፡፡
ይህም በተለያዩ እምነቶች መካከል ላለው መከባበር እንደ ትልቅ ማሳያ ተደርጎ ይቀርባል፡፡












