አንዳንድ ጊዜ ታሪክ በቤተ መፅሐፍት መደርደሪያ ላይ ከተደረደሩ መዛግብትና ሰነዶች ውጪ ይገኛል፡፡ በምንዘዋወርበት ጐዳና፣ በሕንፃዎች፣ በሐውልቶች እና አደባባዮች ላይ ታሪክን ሰፍሮ ልናገኘው እንችላለን፡፡
በጣሊያን ሮም ከተማ ከሚገኘው ማዕከላዊ የባቡር ጣቢያ የሚወጡ መንገደኞች ወይም ሀገር ጐብኚዎች መጀመሪያ የሚያገኙት “ፒያሳ ዲ ቺንኩዊቼንቶ” ወይንም “የአምስት መቶዎቹ አደባባይ” እየተባለ የሚጠራውን ቦታ ነው፡፡ የተወሰኑት መንገደኞች ታክሲዎች እና ሱቅ-በደረቴዎች በሚፈጥሩት ግርግር ምክንያት ለአደባባዩ ምንም ትኩረት ሳይሰጡ አልፈውት ሊሄዱ ይችላሉ፡፡
አንዳንዶቹ ይህ ቦታ የሀገሪቱ ዜጎች በኩራት የሚያወሩለት በ1500 ጣሊያን ደርሳበት የነበረው የሕዳሴ ዘመን ትቶት ያለፈው ቅርስ እንደሆነ ሊገምቱ ይችላሉ፡፡ በመኪና ፍቅር የተለከፉ ሰዎች “ፊያት ቼንኩዊቼንቶ” ከሚለው መጠሪያ ጋር ግንኙነት ያለው መስሏቸው የሀገሪቱን የመኪና ኢንዱስትሪ ወደ ትልቅ ደረጃ ስላደረሰው የፊያት ኩባንያ ቢያስቡ አይፈረድባቸውም፡፡ “ፒያሳ ዲ ቺንኩዊቼንቶ” የኢጣሊያ ጦር በአፍሪካ ምድር ዶጋሊ በተባለ ቦታ ታላቅ ወታደራዊ ሽንፈት ባጋጠመው ጊዜ ለሞቱ አምስት መቶ የኢጣሊያ ወታደሮች መታሰቢያ የተሰራ አደባባይ ነው፡፡
እነዚህ “ዶጋሊ” በተባለ ስፍራ በተደረገ ጦርነት የወደቁ የኢጣሊያ ወታደሮች መስዋዕት የሆኑበት ምክንያት የኦቶማን ቱርክ ኢምፓየር ከሱሊማን ቀዳማዊ የስልጣን ዘመን አንስቶ (ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ) እስከ 18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ለሶስት መቶ አመታት የዘለቀውን በምዕራብ የቀይ ባህር ዳርቻ ከጅቡቲ ባህር ወሰን አንስቶ እስከ ሱዳን የባህር ዳርቻዎችን የሚያካልል ሰፊ ግዛቱን ለማስተዳደር የሚያስችል አቅም በማጣቱ ጣሊያን የተፈጠረውን ክፍተት ለመጠቀም መወሰኗ ነው።
ከጣሊያን የዶጋሊ ድል በኋላ የመጣው የአደዋ ጦርነት የወለደው የአደዋ ድል ነበር። የአደዋ ድል የተገኘው ኢትዮጵያውያን በጋራ የመሩበትና የተዋጉበት ታሪካዊ ጦርነት መሆኑ ይነገራል። የአደዋ ጦርነትን ከመሩት 12 አዛዦች አንዱ ራስ መንገሻ ዮሐንስ አንዱ ናቸው።
ራስ መንገሻ ዮሐንስ የትግራይ አስተዳዳሪ ነበሩ። የተወለዱት በ1857 ዓ.ም. ትግራይ ውስጥ ነው። የንጉሥ ዮሐንስ አራተኛ ልጅ ሲሆኑ፤ እናታቸው ወለት ተክለ ሀይማኖት ይባላሉ። ራስ አርአያ ኃይለስላሴ ዮሐንስ የራስ መንገሻ ዮሐንስ ታናሽ ወንድም ናቸው።
ራስ መንገሻ ዮሐንስ የንጉሥ ዩሐንስ የወንድም ልጅ በመሆን ያደጉ ናቸው። ራስ መንገሻ የንጉሥ ዮሐንስ ልጅ መሆናቸው የተነገረው በመተማ ጦርነት 1882 መሞታቸውን ተከትሎ ነበር። ራስ መንገሻ ዮሐንስ በአደዋ ጦርነት የጣሊያንን ወረራ ከቀለበሱ አመራሮች አንዱ ናቸው።

ራስ መንገሻ ዮሐንስ የአጼ ዩሐንስ ወታደራዊ አዛዥ ጀነራል ራስ አሉላ ጠንካራ የወታደራዊ እና የፖለቲካ ድጋፍ ነበራቸው። በተጨማሪም ራስ መንገሻ ዮሐንስ የዩሐንስ 4ኛ በቁጥር የጦር መሳሪያዎች እና ወታደሮች ወራሽ በመሆናቸው አቅም ጨምሮላቸዋል።
አፄ ዮሐንስ እንደሞቱ እና አፄ ምኒልክ የንጉሠ-ነገስትነቱን ቦታ እንደያዙ ራስ መንገሻ የትግራይ አገረ ገዥነት ተሰጣቸው፡፡ ራስ መንገሻ ዮሐንስ ከአጼ ምንሊክ ጋር የተወሰነ ቁርሾ ነበራቸው። ጣሊያን ሁለቱ ያላቸውን ልዩነት ለመጠቀም ብዙ ሞክራለች። ራስ መንገሻ ዮሐንስ ከአጼ ምንሊክ ላይ እንዲያምጹ ስትሞክር ነበር።
የአደዋ ጦርነት ሲከሰት ራስ መንገሻ ዮሐንስ ከአጼ ምንሊክ ጋር ያላቸውን ልዩነት ወደ ጎን በመተው በሀገራቸው የመጣውን ጠላት በጋራ ለመመከት ተንቀሳቀሰዋል። ራስ መንገሻ ዮሐንስ በአድዋ ዘመቻ ያሰለፉት የሠራዊት ብዛት 12000 ነበር፡፡
ከአድዋ ጦርነት በፊትም ሆነ በኋላ ጣሊያኖች በስተጀርባ ሆነው በንጉሠ-ነገሥቱ ላይ እንዲያምፁ ይገፏፏቸው ነበር፡፡ ምፅዋ ላይ የነበሩት ጣሊያኖች ራስ መንገሻን እንዲያምፁ የሚያደጉርት የስልጣንን ጉዳይ እያነሱ ነበር፡፡ ራስ መንገሻ የጣሊያን ውትወታ አሸንፏቸው በአፄ ምኒልክ ላይ ሸፈቱ፡፡
አፄ ምኒልክም ከራስ መኮንን ጋር ከራስ (በኋላ ንጉሥ) ሚካኤልን፣ ዋግሹም ጓንጉልን እና ደጃዝማች (በኋላ ራስ) አባተን አጋዥ አድርገው “አውቆ እጁን ቢሰጥ ይዛችሁት፤ እምቢ ካለ ውጉት” ብለው ወደ ትግራይ ላኳቸው፡፡ እቴጌ ጣይቱም ደብዳቤ ፅፈው ላኩለት፡፡
ደብዳቤው ቢደርሳቸውም ራስ መንገሻ በሰላም ሊመለሱ ባለመፍቀዳቸው በልዑል ራስ መኮንን የሚመራው ጦር ወደ እደጋ ሐሙስ በመሄድ ከበባ አደረገ፡፡
ጦርነቱ ከመደረጉ በፊትም ራስ መኮንን እና የአባታቸው የአፄ ዮሐንስ የክርስትና ልጅ ከሆኑት ከዚያን ጊዜው ራስ ሚካኤል በሰላም እንዲገቡ በሚል የምክር ቃል ተላከባቸው፡፡
ለውጊያ መዘጋጀታቸው ስለተሰማ ይገኙበት ከነበረው ሥፍራ በስተጀርባ በአጋሜ በኩል አራት ሺህ ባለጠመንጃ ጦር ዘልቆ ሄዶ ጦርነት ገጠማቸው፡፡ የራስ መንገሻም ጦርም ክፉኛ በመጎዳቱ እጃቸውን ሰጡ፡፡ ራስ መንገሻም በአንኮበር አምባ ታስረው ተቀመጡ፡፡
በትዳር ሕይወታቸው የእቴጌ ጣይቱ የወንድም ልጅ ከሆኑት ከጎንደሯ እመቤት ከወ/ሮ ከፋይ ወሌ ብጡል ተጋብተው ወ/ሮ አስቴር መንገሻን፣ ወ/ሮ አልማዝ መንገሻንና ወ/ሮ ብርሃኔ መንገሻን ወልደዋል፡፡
በአንኮበር አምባ ታስረው ባሉበት ወቅት እቴጌ ጣይቱ በክብር ያጋቧቸውን የወንድማቸውን ልጅ ወ/ሮ ከፋይን አፋተው መልሰው ለራስ ናደው ዳሩላቸው፡፡ ራስ መንገሻ እስከ እድሜያቸው ፍፃሜ በእስር ላይ ቆይተው ህዳር 6/1899 ዓ.ም. እዚያው አንኮበር አምባ ላይ እንዳሉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
የአድዋ ድል እንደ ራስ መንገሻ ዩሃንስ ባሉ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የጦር መሪዎች እየተመራ ነጠላትን ጦር ድል አድርጓል። ድሉ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላ አፍሪካ ብሎም የጥቁር ህዝቦች ቀንዲል ሆኖ ዘላለም ይዘከራል።
በ-እስክንድር ከበደ












