በዓለም የጥቁር ህዝቦች የመብት ትግልና የነጻነት ጉዞ መሰረትን የጣለው የአድዋ ድል የአሸናፊነት፣ የአንድነትና ሁሉን አቀፍነት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ኢትዮጵያውያን አርበኞች በዱር በገደሉ ባሳዩት ተጋድሎ ዘመን ተሸጋሪ ድል የተመዘገበበት እንደመሆኑ አድዋ ከትውልድ ትውልድ የሚወራረስ የህብረት ስራ መንፈስ ነው፡፡
በአድዋ ጦርነት ከመላ ኢትዮጵያ የመጡ አርበኞችና ሀገር ወዳድ ዜጎች በ12 የጦር አዝማቾች መሪነት ታላቅ ድል አስመዝግበዋል፡፡ ከእነዚህ የጦር መሪዎች መካከል ራስ አሉላ አባ ነጋ አንዱ ናቸው፡፡
የተናገሩትን ሁሌ ያደርጋሉ፡፡ በጦርነት ግንባርም ከፊት ይቆማሉ፡፡ ፈሪ አይወዱም፤ ጥቃትም አይቀበሉም፡፡ ነፃነታቸውንና የሀገራቸውን ክብር ማስነካት ያማቸዋል፡፡ እንዲህ ነው! ከብዙ በጥቂቱ ታላቁ የአድዋ ጀግና ራስ አሉላ አባነጋ የሚገለፁት፡፡
ራስ አሉላ አባ ነጋ በትግራይ ተንቤን እንደተወለዱ የታሪክ ማህደር ይገልፃል፡፡ ትምህርታቸውንም በእዚያው አካባቢ በሚገኙ ገዳማት እንደተከታተሉ ይነገራል፡፡ አሉላ የጉርምስና ዕድሜያቸውን በአፄ ዮሃንስ አጎት ራስ አርአያ ድምጹ ቤት በአገልጋይነት ጀመሩ፡፡
በስተኋላ ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ፤ ቀጥሎም ወደ አፄ ዮሃንስ 4ኛ ቤት ከተዛወሩ በኋላ ሹመትን በሹመት በመደራረብ ወደ ፊት ገሰገሱ፡፡
በመጀመሪያ በእልፍኝ አስከልካይነት በመቀጠል በአጋፋሪነት ተሾሙ፡፡ ደጃዝማች ካሳ ንጉሰ ነገስት አጼ ዮሃንስ 4ኛ ሲባሉ አሉላ የሻለቅነትን ማዕረግና የንጉስ ሊጋባነትን ማዕረግ ደርበው ያዙ፡፡በጦር ሜዳ ውሎ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያውቋው ሁሉ ስለእርሳቸው ይመሰክራሉ፡፡

ዛሬ ላይ ሆነው ነገር የሚመረምሩ ከራስ በላይ ሀገር የሚያስቀድሙ የኢትዮጵያ ቁርጥ ልጅ ነበሩ ይሏቸዋል፣ ራስ አሉላ አባነጋን፡፡
አጼ ዮሃንስን በጉንዳጉንዲት ጦርነት ጠላትን አንበርክከው ያሳይዋቸው ጀግና አሉላ አባ ነጋ አጠገባቸው መሆናቸውን ሁሌም ይፈልጉታል፡፡
ጠላት ሲገጥማቸው ጦራቸውን በልበ ሙሉነት እንዲመሩ ኃላፊነቱን ለራስ አሉላ አባነጋ ይሰጧቸዋል፡፡
አሉላም – አያቴ ወታደር ናቸው፣ አባቶቼም እንዲሁ፡፡ እኔም ወታደር ነኝ፡፡ ያገር ዳር ድንበርና ልዑላዊነትን ከወራሪ ጠላት የምጠብቅ ወታደር ነኝ፡፡ እኔ በህይወት እያለሁ ሀገሬ በውጭ ወራሪ ኃይሎች አትደፈርም፡፡ በማለት ቃላታቸውን ለሀገራቸው ሰተዋል፡፡
በሰሜን በኩል ኢትዮጵያን ለመግዛት ቋምጦ የመጣውን የኢጣልያ ጦር ምፅዋ ላይ ሊገጥሙ ተዘጋጁ፡፡ በሰዓቱ የመሸገውን የፋሽት ኃይል ከአስመራ ተነስቶ በመሄድ በከበባ ውስጥ ከከተቱት በኋላ በዚኁ ድንበር ጥሶ የገባው የጠላት ኃይል በጦሩ ጀግና ራስ አሉላ አባ ነጋ መሪነት ድባቅ ተመታ፡፡
በጦርነቱ ከአምስት መቶ በላይ የኢጣልያ ጦር ተማርኳል፡፡ አጼ ሚኒሊክም በልዩ የጦር አማካሪነት ሲያገለግሉ የቆዩት ራስ አሉላ አባነጋ ኢትዮጵያን ሊወር የመጣውን ፋሺት ጀግንነት ሊገጥሙ መስዋትነት ሊሆኑ ተዘጋጁ፡፡
በሺዎች የሚቆጠር ጦር ያሰለፈው ጄነራል ባራቶሪ አምባላጌንና መቀሌን ሊቆጣጠር የጦር ስልት ነደፈ፡፡ ወዲያው መቀሌ መሽጎ የነበረው የጠላት ጦር ወደ አድዋ ተራራ እያመራ መሆኑን መረጃ የደረሳቸው ራስ አሉላ አባ ነጋ ጦራቸውን አሰልፈው ከሶሎዳ ተራራ ጀርባ መሸጉ፡፡
በየካቲት 23 ቀን 1888 ከጀግኖቹ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ጋር በዚያው በመሸጉበት ሶሎዳ ተራራ የመጨረሻውን ውጊያ ከጄነራል ዳቦር ሜዳም ጦር ጋር አደረጉ፡፡
በሀገር ለመጣ የማይመለሱት ራስ አሉላ አባነጋ የገቡትን ቃል በመጠበቅ፤ ያላቸውን የጦር ስልት በመጠቀም፤ የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን የጄነራል ዳቦር ጦርን ደመሰሱ፡፡
በተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ ጀብዱ የፈፀሙት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ የሀገር ባለውለታነታቸው በጦር ሜዳ ብቻ አልነበረም፡፡ በዲፕሎማሲ፣ በፍትህ፣ ደግሞም የሀገር ዳር ድንበር የሚጠብቀው ሠራዊት ደመወዝ እንዲከፈል ያደረጉ ታላቅ ስብዕና ነበሩ፡፡
አሉላ አባ ነጋ በልባቸው የነገሰውን የሀገር ፍቅር ስሜት ፍትህና ድል ማድረግን የህይወታቸው መርህ አድርገው እስከ መረብ ድረስ ሲጓዙ ቀይተው የካቲት 9 ቀን 1889 አረፉ፡፡
በዚህ ወቅት ድሮም ስለጀግንነታቸው የመሰከረው ጠላት “ጎራዴውን ወደኛ እንደመዘዘ፤ ሳይመልሰው አሉላ ሞተ!” ሲል ገልጿቸዋል፡፡
በ-አብይ ሃብታሙ












