አዲስ አበባ | የካቲት 20፣ 2016| NBC ETHIOPIA -የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡ የመላው ጥቁር ህዝብ ሰብዓዊ ክብር የታደሠበት፤ በእውነትና በፍትህ፣ በህልውናና በሀገር ክብር ዳግም የታነጸበት ነው፡፡
የአድዋ ድል ከመላው ሀገሪቱ የተወጣጡ 12 የጦር መሪዎች ጦራቸውን አደራጅተውና ስንቃቸውን ቋጥረው ጉዟቸውን ወደ አድዋ አድርገዋል፡፡ የራስ ብጡል ኃይለ ማርያም የበኩር ልጅ፤ የጣይቱ ብጡል ታናሽ ወንድም፤ የራስ ጉግሳ ወሌ አባት ከ12 ቱ የጦር መሪዎች አንዱ ናቸው፡፡ ‹‹አባ ጠጣው››… ራስ ወሌ ብጡል!
የሰሜን ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ የነበሩት የራስ ወሌ አባት ውቤ ኃይለ ማርያም በ1831 ዓ.ም ትግራይን በመውረር የአያት ቅድመ አያታቸው የነበረውን የሰሜን አውራጃን እስከ 1855 ዓ.ም ድረስ ሲገዙ ቆዩ።
በወቅቱ የሀገሪቷ መሪ የነበሩት በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ ተብለው የሚታወቁት በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ወታደርና ፖለቲከኛ አጼ ቴዎድሮስ ነበሩ። የራስ ውቤ ኃይለ ማርያም ወንድም ራስ ብጡል ኃይለ ማርያም ሁለት ልጆቻቸው ወሌ እና አሉላ በ1857 ዓ.ም ገደማ በአምባ ማርያም ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ በእስር ግዞት ስር ካስቀመጧቸው ሰዎች መካከል ነበሩ።
ወሌ ብጡል በመቅደላ፣ በአምባ ማርያም እና በደብረታቦር ሳሉ ነበር ከሸዋ ልዑል ዳግማዊ ምኒልክ ጋር የተዋወቁት። አጼ ምኒልክ በ1857 ዓ.ም ከመቅደላ አምባ አምልጠው ወደ ሸዋ ከገቡ በኃላ በነሀሴ 24 ቀን 1857 ዓ.ም በአባታቸው ዙፋን ላይ ነገሱ፡፡
እንግሊዝ ወደ አቢሲኒያ ያደረገውን ዘመቻ እንደ መልካም እድል በመጠቀም ወሌ ከአሉላ ጋር ከአምባ ማርያም እስር አምልጠው ወደ ሸዋ ሸሹ።
ምኒልክ የሸዋ ንጉስ ተብለው ስልጣን ከጨበጡ ከሁለት አመታት በኃላ ወሌ ከወንድማቸው ከአሉላ ጋር ከአጼ ምኒልክ ጋር መኖር ጀመሩ፡፡ በዚህም ወሌ ብጡል የደጅ አዝማችነት፤ አሉላ ደግሞ የፊታውራሪነት ማዕረግን አገኙ። በ1876 አጼ ምኒልክ ወሌን የየጁ አስተዳዳሪ አድርገው ሾሙ፡፡ ወሌ ብጡል የደጅ አዝማችነት ማዕረግን ካገኙ ከስድስት አመታት በኃላ ታላቅ የፖለቲካ ክስተት ተፈጠረ። በ1883 የወሌ እህት ጣይቱ ብጡል ከንጉስ ምኒልክ ጋር በትዳር ተሳሰሩ፡፡

ከጋብቻቸው በኋላ ደጅ አዝማች ወሌ በአገልግሎታቸውም ሆነ በአማችነታቸው ስለተደሰቱ ምኒልክ ንጉሰ ነገስት ከሆኑ በኋላ የራስነት ማዕረግ አግኝተው ታላቅ ባለሟል ሊሆኑ ችለዋል። እ.ኤ.አ. በ1889 ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ከሆኑ በኃላ የደጃዝማች ወሌን ግዛት አስፋፍተው በጌምድርን ጨምረው የራስነት ማዕረግን ሰጧቸው።
ራስ ወሌ በአንደኛው ኢታሎ-ኢትዮጵያ ጦርነት በአምባ አላጌ፣ በመቀሌ እና በአድዋ ጦርነት ላይ ከፍተኛ ጀብዱ ፈጽመዋል። “አስር ደጅ አዝማች የደገሰውን፤ የወሌ ፈረስ ጠጣው ብቻውን!” የተባለላቸው ራስ ወሌ በአምባላጌ በተደረገው ውጊያ ላይ የራሳቸውን 10ሺ ሰራዊት በማሰለፍ ድል በማድረግ ታላቅ ጀብድ እና አኩሪ ገድል አስመዝግበዋል፡፡
ወደ አድዋ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር 120ሺ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ጠቅሰዋል፡፡ ራስ ወሌም የጥቁር ህዝቦች ድል በሆነው የአድዋ ጦርነት ከበጌምድር፣ የጁ፣ ዋድላ እና ዳውንት የተውጣጣውን ሰራዊታቸውን በመያዝ በጦርነቱ ተዋግተዋል፡፡ ከግዛታቸው 10ሺ የሚደርሱ እግረኛ ወታደሮችን አሰልፈዋል። በአድዋው ጦርነት ቅድሚያ ከተላኩት የጦር አበጋዞች መካከል ግንባር ቀደሙ ራስ ወሌ ናቸው፡፡
ራስ ወሌ ከሰራዊታቸው ጋር እስከ መጨረሻው የአድዋ ድል ድረስ በጀግንነት ለሀገራቸው መስዋዕትነት የከፈሉ ሲሆን ለየጁ ባላባት ለራስ ወሌ ብጡል ስለ ጀግንነታቸው ታዋቂው አዝማሪ ሀሰን አማኑ እንዲህ ሲሉ ገጥመውላቸዋል፡፡
“ሰባት ደጃዝማች ዐሥር ፊታውራሪ የጠመቀውን
የወሌ ፈረስ ጠጣው ብቻውን፣
ወሌ በቡሎ ዘሎ ሲወጣ
ይመስላል ሐምሌ ክረምት የመጣ፣
ወሌ ወሌ ወሌ ቢሏችሁ
የሳቱ ጒማጅ መርጦ አለላችሁ፣
የወሌ ፈረስ ቀጭኑ ቡሎ፣
ዥራቱ አውሳ ግንባሩ ወሎ!”
ንጉሰ ነገስት አጼ ምኒልክ ባጋጠማቸው የጤና እክል ሳቢያ በ1906 ዓ.ም ህይወታቸው አለፈች፡፡ በንጉሱ ሞት የተነሳ በስልጣን መንበሩ ዙሪያ ከፍተኛ ክስተተቶች ተስተናግደዋል፡፡ ባለቤታቸው ንግስት ጣይቱ ከስልጣን ሲወርዱ ራስ ተሰማ ናደው በበላይነት ስልጣኑን ያስተዳድሩ ጀመር፡፡ የእህታቸው ከስልጣን መገፋት ስላበሳጫቸው ለእቴጌ ጣይቱ ከስልጣን መወገድ ከሸዋ መኳንንት ጋር በማበር አስተዋጥዖ አድርገዋል ብለው ከጠረጠሯቸው ከወሎው ገዢ ራስ ሚካኤል ጋር ጠብ ፈጠሩ፡፡
ከገዢው ወታደሮች ጋር ከሰኔ እስከ ህዳር ድረስ ለስድስት ወራት ከፍተኛ ውጊያ አካሄዱ፡፡ በስተመጨረሻ በራስ ወሌ የሚመራው ጦር ሽንፈትን ቀመሰ፡፡ ራስ ወሌም እጃቸውን በመስጠት ቀሪውን ህይወታቸውን በእስር አሳልፈዋል፡፡
የአድዋው አጋፋሪ፣ የየጁና የበጌምድር ባላባት፣ የጣይቱ ብጡል ታናሽ ወንድም ራስ ወሌ ብጡል እህታቸው ከሞቱ ከሶስት ወራት በኃላ በግንቦት ወር 1910 ዓ.ም በእስር ላይ ሳሉ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፡፡
ራስ ወሌ ብጡል ህይወታቸው ቢያልፍ በአድዋ ጦርነት ወቅት ከነበሩት 12ቱ የጦር መሪዎች ጋር በመሆን የፈጸሙት የዓድዋ ላይ ጀብዱ ለዘላለም ሲታወስ ይኖራል፡፡
በ-ሐሴት ሀይሉ












