አዲስ አበባ | ታህሳስ 30፤ 2016| NBC ETHIOPIA -የጉሮሮ ህመምን ከሚያስከትሉ ምክንያቶች መካከል በተለያዩ ተዋህስያን ኢንፌክሽን ምክንያት የሚመጡ እንደ ቶንሲል ህመም ያሉ በሽታዎች ዋነኞቹ ሲሆኑ አለርጂ፣ የጉሮሮ መድረቅ፣ በጣም ሙቅ የሆኑ ምግቦች ወይም መጠጦችን መውሰድ እና ድምፅን አብዝቶ መጠቀም የመሳሰሉ ምክንያቶች ደግሞ አነስተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።

የቶንሲል ህመም

ቶንሲሎች በአፋችን የኋላ ክፍል ከእንጥል በግራና በቀኝ በኩል የሚገኙ እጢዎች ሲሆኑ ጥቅማቸውም ከምንመገባቸው ምግቦችና ከምንተነፍሰው አየር ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ ጎጂ ተዋሲሀንን እንደመጀመሪያ መከላከያ መንገድ ሆኖ ማገልገል ነው፡፡ የእነኚህ ቶንሲሎች በኢነፌክሽን መጠቃት በተለምዶ “ቶንሲል” የምንለውን ህመም ያስከትላል፡፡ የቶንሲል በሽታ ማንኛውንም ሰው ሊያጠቃ ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ በትምህርት መግቢያ እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ህፃናትን ያጠቃል፡፡
የቶንሲል በሽታ መንስኤው ምንድን ነው?

ቶንሲል በተለያዩ ምክንያቶች ሊቆጣ ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ ግን በቫይረስ ወይም ባክቴሪያ ምክንያት በሚመጣ ኢንፌክሽን ይታመማል፡፡ አብዛኛው (25-45%) የሚሆነው የቶንሲል በሽታ በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ ሲሆን ባክቴሪያ በተለይም ግሩፕ ኤ ስትሬፕቶኮከስ (Group A streptococcus) የተባለው ባክቴሪያ ቀጣዩን ደረጃ ይይዛል፡፡
የቶንሲል በሽታ መተላለፊያ መንገዶች ከጉንፋን እና መሰል የመተንፈሻ አካላት በሽታ መተላለፊያ መንገዶች ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ እነዚህም በሽታው ያለበት ሰው በሚያስልበት ወይም በሚያስነጥስበት ጊዜ በቅርበት መሆን፣ በቀጥታ ንክኪ ማለትም ንፁህ ባለሆኑ እጆች መጨባበጥ ወይም በተዋህስያኑ ከተበከሉ ግዑዝ ነገሮች ንክኪ ናቸው፡፡
የቶንሲል በሽታ ምልክቶች

የቶንሲል በሽታ ምልክቶች እንደ አምጪው ተዋህስ አይነት ይወሰናል፡፡ በምልክቶች ብቻ በእርግጠኝነት በባክቴሪያ ወይም በቫይረስ ነው የመጣው ብለን መደምደም ባንችልም በአብዛኛው
ከቫይረስ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ቶንሲል በሽታ፡-
-ቀስ በቀስ የመጀምር
-አብሮ ተያይዞ ሳል ወይም ጉንፋን መሰል ምልክቶች የማሳየት
-የቶንሲል መቅላት እና ማበጥ
-ቀለል ያለ ትኩሳት፣ ራስ ምታትና ብርድብርድ የማለት ምልክቶችን ያሳያል
-በሌላ በኩል በባክቴሪያ ምክንያት የሚመጣ የቶንሲል ህመም
-በአጭር ጊዜ ውስጥ(በፍጥነት) የመጀመር
-በከፍተኛ ሁኔታ ለመዋጥ የመቸገር
-የቶንሲል መቅላት፣ ማበጥና አልፎም መግል የመያዝ
-አንገት ላይ ያሉ እጢዎች (Lymph nodes) የማበጥ
-ከፍተኛ የሆነ ራስ ምታት፣ ትኩሳትና ብርድ ብርድ የማለት ምልክቶችን ያሳያል፡፡
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት











