አዲስ አበባ | ታህሳስ 23፤ 2016| NBC ETHIOPIA – ጀርመናዊው የ2 ጊዜ የባሎን ደ’ኦር አሸናፊ ፍራንዝ ቤከንባውር ውስብስብ የጤና ሁኔታ ውስጥ መግባቱ ተሰምቷል።

የጀርመኑ ተነባቢ ጋዜጣ ዴር ስፒግል እንደዘገበው፣ የ78 ዓመቱ ቤከንባውር ለረጅም ወራት በተደራራቢ የጤና እክሎች ሲሰቃይ የቆየ ሲሆን አሁን ላይ አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ወንድሙ ዋልተር ፍራንዝ፣ “አሁን ደህና ነው ብየ ብናገር ዉሸት ይሆንብኛል፣ መዋሸት ደግሞ አልፈልግም። እርሱ በጥሩ ሁኔታ ላይ አይገኝም፣ በተለይም ከሚያዚያ ወር ወዲህ በጠና ታሟል” ብሏል።
የሰውነት ውፍረት መጨመርና ትውስታን የማጣት ችግር ውስጥ መግባቱን አክሏል። ቤከንባውር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለተደራራቢ የጤና ችግር መዳርጉ ሲነገር የቆየ ሲሆን ሁለት የልብ ቀዶ ጥገና እና አንድ የዳሌ ንቅለ ተከላ አድርጓል።
በ2019 የአንድ ዓይኑን ብርሃን ማጣቱን በእራሱ አንደበት ተናግሮ ነበር። በርካቶች “የምንጊዜም ምርጡ ጀርመናዊ የእግር ኳስ ተጨዋች” የሚሉት የ1970ዎቹ ኮኮብ ለአገሩ ሁለት የዓለም ዋንጫዎችን አሸንፏል።

በ1974 በተጨዋችነት በ1990 ደግሞ በአሰልጣኝነት የዓለም ሻምፒዮና ነበር። ውስብስብ የጤና ሁኔታ ውስጥ የመግባቱ ዜና ከተሰማ በኋላ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማሕበረሰብ የበቶሎ ይማርህ መልዕክቱን እያሰተላለፈ ይገኛል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc












