አዲስ አበባ | መስከረም 24 2016| NBC ETHIOPIA -ሀገራዊ ምክክሩ እዚህም እዚያም የሚታየውን ረብሻ በማስቀረት ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር እና የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ተናገሩ፡፡

ፕሮፌሰር በየነ በአሁኑ ወቅት እንደመልካም አጋጣሚ የተገኘው ሀገራዊ ምክክር ሊያመልጠን አይገባም፡፡ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እያካሔደ ያለው ሒደት አበረታች ነው ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ ሌሎቹም ልብ እንዲገዙ የሚረዳም ጭምር ነው፤ ፀጥታ አደፍራሾቹ ሕዝቡ ከእነርሱ ጋር እንዳልሆነም የሚረዱበት እንደሚሆን ተስፋ አለኝ፤ በዚህ አጋጣሚም በጥባጮች ሊጋለጡ ይችላሉ ብለዋል።
ፕሮፌሰር በየነ እንደተናገሩት፤ ምክክር መካሄዱ የሚያሳጣው አንዳች ነገር የለም፤ ይልቁኑንም የሚጨምረው መልካም ነገር በርካታ ነው። ሚዛን የሚደፋው የሕዝብ ቁጥርም በዚህ ምክክር ላይ አሉታዊ የሆነ አቋም አይኖረውም።
ስለሆነም ፀጥታውን የሚያደፈርሱ አካላት ምክክሩ እንዳይካሄድ ቢፍጨረጨሩም እንደስጋት ተወስዶ የቀረበውን መልካም አጋጣሚ ማስመለጥ አይገባም። ለኢትዮጵያ የማይመጥን ገጽታ እያላበሱ ስሟን ለማጠልሸት እንደሚሯሯጡም ጠቁመው፤ ይሁንና ኢትዮጵያ እነሱ ከሚሏት በተቃራኒ ያለች ሀገር ናትና ለዚህ አትበገርም ብለዋል።
ፕሮፌሰሩ እንዳሉት፤ የዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያካሔደች ያለውን ሒደትን የሚያዩት ከራሳቸው ጥቅም አኳያ ነው። አንድ ማወቅ ያለብን ነገር ቢኖር ከኢትዮጵያ ጋር መወዳጀት የማይፈልግ የውጭ ሀገር መንግሥት አለመኖሩን ነው።
ኢትዮጵያ ብትፈርስ የሚጠቀም አይኖርም። የኢትዮጵያ መፍረስ በብዙ የሚያጎድል እንደሆነ መንግሥታት አሳምረው ያውቁታል ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ፣ በጠቅላላ በአፍሪካ እና በዓለምአቀፉ ዘንድ ተፈላጊ ሀገር ናት ብለዋል።
ለዚህ የሚሆን ማሳያ የቅርቡን ብቻ ማስታወስ በቂ ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ በአህጉራችንም ሆነ በሌላ አህጉር በኢኮኖሚያቸው የሚበልጡና ሊመረጡ የሚችሉ ብዙዎች እያሉ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን መመረጧ ተፈላጊነቷን የሚያሳይ ነው ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












