አዲስ አበባ | መስከረም 14 2016| NBC ETHIOPIA -ሕዝበ ሙስሊሙ የነብዩ መሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) መውሊድ በዓል ሲያከብር ያለውን በማካፈልና በመረዳዳት ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱልከሪም ሼህ በድረዲን እንደገለጹት፤1498ኛው የነብዩ መሐመድ መውሊድ በዓል መስከረም 16 የሚከበር ሲሆን፤ ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር ያለውን በማካፈልና በመረዳዳት ሊሆን ይገባል።
1498ኛው የነብዩ መሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) መውሊድ በዓል “የይቅርታው ነብይ” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ መርሀ ግብሮች በአንዋር መስጂድ ይከበራል ያሉት ሼህ አብዱልከሪም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበር በዓል በመሆኑ በመተሳሰብና በመተዛዘን እንዲሁም ያለንን በማካፈል ማክበር ይገባል ብለዋል።
ነብዩ መሐመድ በእስልምና ሃይማኖት በነበራቸው አስተምህሮ የሰው ልጆች ያለዘርና የሃይማኖት ልዩነት የምድር ፍጡራን ሁሉ እኩል መሆናቸውን ሲያስተምሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በዓሉ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አባላት፣ ታላላቅ የሃይማኖት አባቶች መምህራን፣ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ረቡዕ መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም በታላቁ አንዋር መስጂድ በድምቀት እንደሚከበር መግለፃቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












