በአዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22/2015፣ NBC ETHIOPIA -የጉምሩክ ኮሚሽን ከነሀሴ 12 ቀን እስከ 18/2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 151 ነጥብ 9 ሚሊዮን የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 120 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የወጭ፤ በድምሩ 272 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውን አስታወቀ፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡
በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር የላቀ አፈጻጸም የተመዘገበ ሲሆን በዚህም ሞያሌ፣ አዲስ አበባ ኤርፖርት እና ድሬድዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡
በቅደም ተከተላቸውም 55 ሚሊዮን፣ 26 ሚሊዮን እና 22 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ ችለዋል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ ሲሆን የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋዉሩ የተገኙ 14 ግለሰቦች እና ስምንት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች ፣ የክልልና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ህዝባችን ምስጋናውን ያደርሳል፡፡
የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪው ማቅረቡን ኢፕድ በዘገባው አስታውቋል፡፡
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc/