አዲስ አበባ ሐምሌ 7፤ 2015 | NBC ETHIOPIA-በሱዳን ምእራብ ዳርፉር ግዛት ቢያንስ 87 የሱዳን ንፁሀን ዜጎች በጅምላ መቃብር መቀበራቸውን የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ቢሮ (OHCHR) አስታውቋል።

ባለፈው ወር በትንሹ የ87 የማሳሊት ብሄረሰብ እና ሌሎች በምዕራብ ዳርፉር በፈጣን ድጋፍ ሃይሎች እና አጋራቸው ታጣቂዎች ተገድለዋል የተባሉ አስከሬኖች ከክልሉ ዋና ከተማ ኤል-ጄኔና ወጣ ብሎ በሚገኝ የጅምላ መቃብር እንደ ተቀበሩ OHCHR በመግለጫው ተናግሯል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመብት ቢሮ ምንጮችን ጠቅሶ እንዳስታወቀው እኤአ በሰኔ 20 ቀን 37 አስከሬኖች በምዕራብ ኤል-ጄኔና በአል-ቱራብ አል አህመድ አካባቢ በሚገኝ አንድ ሜትር ጥልቀት ባለው የጅምላ መቃብር ተቀብረዋል። “ሌሎች 50 አስከሬኖች እኤአ በሰኔ 21 ቀን በዚያው ቦታ ተቀብረዋል” OHCHR አክሎም “የሰባት ሴቶች እና የሰባት ልጆች አስከሬን ከተቀበሩት መካከል እንደሚገኝ” በመግለጫው ገልፃል።
በቀረበው ክስ ላይ ከRSF ፓራሚትሪ ቡድን እስካሁን የተሰጠ አስተያየት የለም። ሱዳን ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በጦር ኃይሉ እና በአርኤስኤፍ መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ወደ 3,000 የሚጠጉ ንፁሀን ዜጎችን ህይወት ሲያሳጣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቆስለዋል ሲሉ የአካባቢው የህክምና ባለሙያዎች ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በሱዳን አሁን ባለው ግጭት ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል ብሏል።
ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በሱዳን እየተካሄደ ያለው ግጭት ወደ ከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ሊመራ እንደሚችል ማስጠንቀቃቸው የሚታውስ ነው።
በሃና ተሰማ
ምንጭ(አናዱሉ)
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia











