
አዲስ አበባ |የካቲት 15 2015 | NBC ETHIOPIA- የቀድሞው በሩሲያ የአሜሪካ አምባሳደር፤ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን በድርድር ለመፍታት ፍላጎት እንደሌላቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።
ሞስኮ በኪዬቭ ላይ ወረራ ስትከፍት የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ጆን ሱሊቫን፤ ጦርነቱ እንዳይጀመር ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ለማድረግ ቢጥሩም “ምላሽ አላገኘሁም” ይላሉ።
አሜሪካዊው ዲፕሎማት አክለው ፑቲን “ከጦርነቱ በፊት ለድርድር ዝግጁ አልነበሩም፤ አሁንም ፈቃደኛ አይደሉም” ይላሉ።
የአሜሪካ መንግሥት ከድርድር ይልቅ ለዩክሬን ዓለም አቀፍ ድጋፍ በማሰባሰብ የጦር ኃይሉን መገንባትንና ሩሲያ ላይ ማዕቀብ መጣልን አልፎም ቢሊዮን ዶላሮች የሚያወጡ የጦር መሣሪያዎችን ለዩክሬን መለገስ መርጧል።
ፑቲን ማክሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር ጦርነቱን ያስጀመሩት ምዕራባዊያን ናቸው ሲሉ ሌሎችን ተጠያቂ አድርገዋል።
ምዕራባዊያን ዩክሬንን ተጠቅመው “ሞስኮን ለመርታት አልመዋል፤ ሩሲያ እንጂ ዩክሬን አይደለችም ለኅልውናዋ የምትታገለው” ብለዋል።
የቀድሞው አምባሳደር እንደሚሉት ፑቲን ዩክሬን ውስጥ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መሪ በተለይ ደግሞ እንደ ዜሌንስኪ ያለ ግለሰብ እንዲኖር አይፈልጉም።
“ዩክሬን ውስጥ መንግሥት እስካለ ድረስ ደስተኛ አይሆኑም። ምክንያቱም ለሩሲያ አደጋ ነው ብለው ስለሚያስቡ። ታላቋ ሩሲያን ለመገንባት ያላቸው ሕልም እውን እንዳይሆን ስጋት ይሆናል ብለው ስለሚያስቡ።”
አምበሳደሩ እንደሚሉት ፑቲን ይህን ጦርነት እንዲያቆሙ ከተፈለገ “ይህን ጦርነት እንደማያሸንፉ ማሳመን ግድ ይላል።”
“ይህን ጦርነት ማሸነፍ እንደማይችል እስኪያስብ ፕሬዝዳንት ፑቲን ድረስ ጥቃቱን ይቀጥላል። ጦርነቱን ደግሞ የሚያሸንፍበት መንገድ የለም። አሁን ባለንበት ሁኔታ ጦርነቱ ጭራሽ አልተጠናቀቀም።”
ሱሊቫን እንደሚሉት የሩሲያው መሪ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ስላላቸው “በቀላሉ እጅ ይሰጣሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው።”
እሳቸው እንደሚያምኑት የዩክሬን ሕዝብም በቀላሉ የሚረታ አይደለም። “የዩክሬን ሕዝብ ይቅርታ የሚያደርግና የሚረሳ አይደለም። ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ጦርነቱ አገባዶ ድንበር አሳልፌ እሰጣለሁ ቢል እንኳ የዩክሬን ሕዝብ አይቀበለውም።”
ይህን የመሰለ የወታደር፣ የፖለቲካ እና የርዕዮተ ዓለም ፍጥጫ ባለበት ሁኔታ ዩናይትድ ስቴትስ ለረዥም ጦርነት መዘጋጀት አለባት የሚል ምክር አላቸው።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ወደ ኪዬቭ ያልተጠበቀ ጉብኝት በማድረግ የአሜሪካ መንግሥት ለዩክሬን ያለውን ድጋፍ አሳይተዋል። ሱሊቫን ጦርነቱ በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል የሚል እምነት የላቸውም።
ሃና ተሰማ
ምንጭ(ቢቢሲ)
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት