
አዲስ አበባ |የካቲት 15 2015 | NBC ETHIOPIA- በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በአጠቃላይ እንደ አገር አቀፍ 12ተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከወሰዱ 896 ሺህ 5 መቶ 20 ተፈታኞች መካከል የማለፊያ ነጥብ በማስመዝገብ 3 ነጥብ 3 በመቶዎቹ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ማለፋቸዉ ይታወቃል፡፡
ይህ ዉጤት በርካታ ስራዎች በትምህርት ዘርፉ ላይ መሰራት እንዳለበት አመላካች ነዉ፡፡
ከዚህም ጋር በተገናኘ መልኩ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚገቡ የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች ከመፈተናቸዉ በፊት ከ8ተኛ ክፍል በኋላ ተከታታይ የተማሪዉን አቅም የሚያጎለብቱ ወጥ የሆኑ ፈተናዎች ቢሰጥ ከትምህርት ጥራትና ከፈተና ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ማቃለል ይቻላል የሚሉ ሃሳቦቸ ይነሳሉ፡፡ አገር አቀፍ ፈተናዎች ቢቀር እንኳን ከተማ አቀፍ እና ክልል አቀፍ ፈተናዎች ቢዘጋጁ ተማሪዉ ጠንካራ ዝግጅትና እውቀት ይኖረዋል ይላሉ ያነጋገርናቸዉ መምህራንና ተማሪዎች፡፡
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ተማሪ እንዲያልፍ እና እዉቀት እንዲኖረዉ ተከከታታይ ወጥ ፈተና ወሳኝ እንደሆነ ይነሳል፡፡
ጣቢያችን ያነጋገራቸዉ መምህራንና ተማሪዎች ከ 8 ተኛ ክፍል በኋላ ያሉ የዘጠኝ ፣አስር እና አስራአንድ ላይ ከተማ አቀፍ ወይም ክልል አቀፍ ፈተናዎች ቢዘጋጁ ተማሪዉ ጠንካራ እንዲሆን አይነተኛ መፍትሄ ነዉ ብለዋል፡፡
ይህን መሰል ፈተናዎች ቢዘጋጁ ተማሪዎች ለ12ተኛ ክፍል የሚኖራቸዉ አቅም የሚያጎለብት እንደሆነና በኩረጃ ላይ የሚነሱትን ቅሬታዎች መልስ ሰጪ ነዉ፡፡ እስከዛሬ የመጣንበት የኩረጃ ልምድን በማስቀረት ጠንካራ ተማሪዎች እንድንሆን ያደርገናል ፡፡ ነገር ግን አሁን በድንገት ወደ አዲሱ የፈተና አሰጣጥ መግባታችን ከባድ ነዉ ይላሉ ተማሪዎች፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ስራዎች ሲሰሩ የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት የሆኑት ተማሪዎች ቢሆኑም ከሚደረጉ ፈተናዎች ዉጪ የመማር ማስተማር ሂደቱን መዳሰስ ተገቢ ነዉ ይላሉ የረዥም አመት የመምህርት ልምድ ያላቸዉ መምህር ታደሰ፡፡
መምህሩ የትምህርት ተቋማት የያዙትን እቅድ ተፈፃሚ ለማድረግ ሲሰሩ የትምህርት ጥራት እንዲኖር ተማሪዎች ዝቅተኛ ዉጤት ሲያመጡ ትኩረት አድርጎ ልጆቹ ላይ መስራት ነዉ እንጂ በዝምታ ሊያልፉ አይገባም ብለዋል፡፡

8ተኛ ክፍል ከክልል አቀፍ ይልቅ አገር አቀፍ ሆኖ ቢሰጥ የበለጠ የትምህርት ጥራቱን ያስተካክላል ተማሪዎችም አቅማቸዉን መመልከት እንዲችሉ ያደርጋል የሚሉም አልጠፉም፡፡
ስምንተኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ቢሆን ተማሪዎች ካሉበት ክልል እና ከተማ በዘለለ አገር አቀፍ እዉቀት እንዲኖራቸዉና ለቀጣይ የመሰናዶ ትምህርታቸዉ ሚናቸዉን እንዲለዩ ያደርጋል ይላሉያነጋገርናቸው መምህራንና ተማሪዎች ፡፡ በዘንድሮ አመትም የ12ተኛ ክፍል ፈተና የማለፊያ ነጥብ ያላስመዘገቡ ተማሪዎች በነጥባቸዉ ተለይተው የዩኒቨርስቲ የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲወስዱ መደረጋቸው ከኢኮኖሚያዊ ጫና ባሻገርም በተማሪዎቹ ላይ የስነልቦና ችግር ይኖረዋል ይላሉ፡፡
ወደ ዩኒቨርስቲ ገብተዉ ማጠናከሪያ ወስደዉ ለፈተና መቅረባቸዉ ካልቀረ በተማሩበት የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ቢወስዱ ይሻላል፡፡ እንደዉም የእኛዉ ተማሪዎች በመሆናቸዉ ዝቅተኛ ያመጡትን ትምህርት በቁጭትና በእልህ ጠንክረን አስተምረን እንዲፈተኑ እናረጋቸዉ ነበር ይላሉ መምህር ሻምበል አባተ የጥቁር አንበሳ የባይሎጂ አስተማሪ፡፡
በሰላም ይልማ
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት