
አዲስ አበባ |የካቲት 13 2015 | NBC ETHIOPIA-አፍሪካ አቀፍ የሠላምና ጸጥታ መፍትሔን ማጎልበት እና አህጉራዊ የኃይል አቅርቦትን ማሳለጥ ከሕብረቱ ቀጣይ አጀንዳዎች መካከል መሆናቸውን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽነሮች አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ እና ዶክተር አቡ ዘይድ አማኒ ተናገሩ።
36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች መደበኛ ጉባዔው መዝጊያ ላይ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሰላምና ፀጥታ እና የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነሮች ያለፉት ዓመት ክዋኔ እና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሰላም እና ፀጥታ ዘርፍ ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ በዘንድሮው የመሪዎች ጉባዔ በኢትዮጵያ ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ትልቅ አድናቆት የቸረ ነው ብለዋል።
የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካ መፍትሔ ማዕቀፍ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል በኢትዮጵያ መንግስትና በሕወሓት መካከል የተደረሰው ስምምነት ትልቁ ስኬት ተብሎ በጉባዔው መነሳቱን ጠቅሰዋል።
አፍሪካ ሕብረትን ወክለው ለስምምነቱ ዕውን መሆን የመሪነት ሚና የተወጡትን አሊሴጎን አባሳንጆን ጨምሮ የድርድር ሂደቱ ተዋናይ የሀገራት መሪዎች እና ለተፈፃሚነት ቀና ትብብር ላሳዩ ኢትዮጵያያን ምስጋና ችረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አፍሪካ የሰላምና ፀጥታን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በመንግስታቱ ድርጅት በኩል በቂና ተመጣጣኝ የፋይናንስ ድጋፍ እንደምትሻም ተናግረዋል።
የሰላም ማስከበር ስምሪቶች ስኬታማነት ፋይናንስና በጀት ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠውና እንደ ፀጥታ ምክር ቤት አፍሪካም የራሷ አቅሙ የጎለበተ ተቋም መገንባት እንደሚጠበቅባት ስለመነሳቱም ጠቅሰዋል።
መፈንቀለ መንግስትን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የተከሰቱ ችግሮች ውይይት እንደተደረባቸው ገልፀው፤ ኢ-ሕገ መንግስታዊ አካሄዶችን ህብረቱ አሁንም በፅኑ እንደሚያወግዝ አንስተዋል።
አፍሪካ በአንድ ድምፅ መቆም እንዳለባት ገልፀው፣ ለዚህ ቀጣናዊ ትብብር እንደሚያስፈልግም ኮሚሽነሩ አንስተዋል።
በጉባኤው በአፍሪካ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን በግጭት አፈታት ሂደቶች የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ጉዳይ ሌላው በመሪዎች ጉባዔ የተወሰን ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በግጭት አፈታተ ሂደት ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉንም ህብረተሰብ ክፍል ማሳተፍ፣ አሳቢያንንና ምሁራንን ጥምረት በመፍጠር ተግባርና ንድፈ ሀሳብን በማጣጣም ውጤታማ ስራ ማከናወን እንደሚገባም አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡
ሰላምና ፀጥታ ከአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ጋር ተዳምሮ ለአህጉሪቷ ፈተና መሆኑን ገለፀው፤ ለመፍትሔው የፀጥታ ተቋማት የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል ነው ያሉት።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር ዶክተር አቡ ዘይድ አማኒ ደግሞ በሃይል፣ በትራንስፖርትና በዲጂታላይዜሽን ጉዳዮች መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም አፍሪካ ሁለንተናዊ ዕድቷን ለማረጋገጥ ያላትን የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጭ መጠቀም የሚያስችላት ፍኖተ ካርታ ነድፋ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
ላለፉት ዓመታት በነበሩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ችግሮችና ፖለቲካዊ ክስተት ምክንያት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ክፉኛ መጎዳቱንም አስታውሰዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ በተሰሩ ቅንጅታዊ ስራዎች እንደ አህጉር መልካም ውጤቶች እንደተመዘገቡም ጠቅሰዋል።
በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዘርፍ አፍሪካ ከፍተኛ እጥረት እንዳለባት ገልፀው፤ ችግሩን ሁሉም ሀገራት የኃይል አማራጫቸውን አሟጠው በሚጠቀሙበት ስትራቴጂ እየተመራች መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በታዳሽ ሃይል ረገድ የግሪን ሀይድሮጂ የኃይል አማራጭን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ገልጸዋል።
የኃይል አቅርቦት ችግርን ለመፍታት አፍሪካ አቀፍ አንድ የኤሌክትሪክ ኃይል ገበያ እንዲኖርም ፍኖተ ካርታ መቀረፁን አስታውሰው፣ ይህም በዓለም ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ገበያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ትልቅ ተግዳሮት የሆነውን የአቪየሽን ነዳጅ የአቅርቦት ክፍተት በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑም ጠቅሰዋል።
ለአፍሪካዊያን ትስስር ቁልፍ ጉዳይ ነው ባሉት የትራንስፖርት ዘርፍም በ35 ሀገራት የአንድ የአየር ትራንስፖርት ገበያ መፈጠሩን ገልጸው፤ በሌሎች የትራንስፖርት አማራጮች ተደራሽ በማድረግ አፍሪካን የማስተሳሰር ስራዎች እንደሚከናውን ጠቁመዋል።
‘የአፍሪካ ኮፕ’ በተሰኘው የ2022 የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ሁሉም ኢኮኖሚ ዘርፎች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር እንዲጣጣሙና እሴት ጭማሪ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ እንደነበር አውስተዋል።
በዲጂታላይዜሽን በኩልም በሁለም መስክ አፍሪካ አቀፍ የጋራ ገበያ እንዲፋጠን የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ የአፍሪካ ዲጂታል መታወቂያ ማዕቀፍን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በጤና፣ በትምህርት፣ በትራንስፖርትና በሌሎች ዘርፎች ላይ የዲጂታላይዜሽን ስትራቴጂ ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን ለማፋጠን የዲጂታላይዜሽን ትግበራው ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ደህንነቱ የተጠበቀና ምቹ የኢንተርኔት አገልግሎት ተደራሽ ማድረግንም ይጠይቃል ብለዋል።
የአፍሪካን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ቻይናን ጨምሮ አህጉሪቷን በሚያስተሳስሩ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከሚያከናውኑ አጋር አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ገልፀዋል።









