
አዲስ አበባ |የካቲት 02 2015 | NBC ETHIOPIA- ቻይና ከምድር ከፍ ብሎ የሚገኝ የጦር መንደር ለመገንባት ውጥን እንዳላት ተነግሯል፡፡
ከሰሞኑ አሜሪካ ሰማይ ላይ የተገኘው ግዙፍ ፊኛ ከህዋ በታች ለምትገነባው የጦር መንደር ዝግጅት ለማድረግ የላከችው ሳይሆን አይቀርም ተብሏል፡፡
ምንም እነኳን አሜሪካ መትታ የጣለችው ቢሆንም በግዙፉ ፊኛ ላይ እየተደረገ ያለው ምርመራ ግን ቀጥሏል፡፡
ቻይና ይህ አዲስ የጦር መንደር በቻይና ወታደራዊ ባለሙያዎችና በዓለም ወታደራዊ ኃይሎች መካከል አስፈላጊ የውድድር መስክ እንደሆነ ታምናለች፡፡ ከወታደራዊ ጄቶች የበረራ ክልል በላይ ከሳተላይቶች በታች በጠፈር አቅራቢያ የሚመሰረተው የጦር ስፍራ የሃይፐርሶኒክ የጦር መሳሪያዎች መሸጋገሪያ እና የባላስቲክ ሚሳኤሎች የሚያቋርጡበት የአየር ክልል ነው ትብሏል፡፡
በፀሀይ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ድሮኖች ፤ ሃይፐርሶኒክ ተሽከርካሪዎችን እና ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የታጠቁ መርከቦችን ከማዘጋጀት በተጨማሪ ቻይና ይህንን ከህዋ በታች ያለ ረቂቅ የጦር መንደር ለመጠቀም ለምርምር ከአስርት አመታት በላይ ያስቆጠሩ የቴክኖሎጂ ግኝቶቿን ማለትም የስትራቶስፌሪክ አየር መርከቦችን እና ከፍታ ላይ ያሉ ፊኛዎችን እየሞከረች እንደምትገኝ ተገምቷል ፡፡
የአሜሪካ ባለስልጣናት ቻይና ከአሜሪካ በተጨማሪ ወደ አምስት አሃጉራት ፊኛዎቹን መላኳንና የፊኛዎቹ ተግባር ስለላና ክትትል ለማድረግ እንደሆነና ይህም የሃገራቱን ሉአላዊነት የጣሰ ተግባር መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡ ቻይና በበኩሏ ፊኛው ለሲቪል ምርምር የሚያገለግል እንደሆነ ተናግራ በፊኛው ላይ የተወሰደውን ወታደራዊ እርምጃን ኮንናለች ። ተንታኞች ሁኔታው ቻይና ከአየር በላይ ላሉ ተሽከርካሪ የጦር አካላት እና ለኤሌክትሮኒካዊ የመከላከያ እርምጃዎች ያላት ፍላጎት እያደገ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል
በዩናይትድ ስቴትስ ላይ በረረ የተባለው የቻይና የሰለላ ፊኛ መውደቅ ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ፉክክር እየተጠናከረ መጥቷል፡፡
የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉት ፊኛው ወደ 200 ጫማ (60 ሜትር) ቁመት ፣ የመጫኛው ክፍሉ በመጠን ከአነስተኛ አውሮፕላን ጋር የሚስተካከል ሲሆን በመቶዎች ምን አልባትም በሺዎች የሚቆጠር ፓውንድ ክብደት እንዳለው ገልፀዋል፡፡
አሜሪካ በግዛቷ ውስጥ ተኩሳ የጣለችው እና የስለላ ነው ተብሎ የተጠረጠረው የቻይና ፊኛ አምስት አህጉራትን ያካለለና ተመሳሳይ ተልዕኮ ያላቸው መርከቦች አካል ነው ብላ እንደምታምን አስታውቃለች።
ቻይና በበኩሏ “የአየር መርከብ” ስትል የገለጸችው ፊኛ የስለላ እንዳልሆነ እና የአየር ንብረት ጥናት የሚሰራ፣ ነገር ግን ባጋጠመው መጥፎ የአየር ጠባይ በድንገት ወደ አሜሪካ ክልል የገባ መሆኑን በተደጋጋሚ አስታውቃለች።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉት ፊኛው ተመትቶ እንዲወድቅ ከተደረገ በኋላ የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት (ፔንታገን) በመከላከያ ሚኒስትር ሊሎይድ ኦስቲን እና በቻይናው አቻቸው መካከል በስልክ ውይይት ለማድረግ ታቅዶ የነበረ ሲሆን ቻይና ግን ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታ ውይይቱ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡
በዚህ የቻይና ፊኛው በአሜሪካ የአየር ክልል መገኘት ምክንያት ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ያስከተለ ሲሆን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለስብሰባ ወደ ቻይና ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ ሰርዘዋል።
ስብሰባው በአሜሪካ እና በቻይና መካከል “ኃላፊነት በጎደላቸው እርምጃዎች” ዙሪያ ለመነጋገር በዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ይካሄዳል የተባለ ከፍተኛ ስብስባ ነበር።
አሜሪካ መትታ የጣለችው ፊኛ ስብርባሪ በደቡብ ካሮላይና ግዛት ማይርትል የባሕር ዳርቻ ላይ ተገኝቷል። የባሕር ኃይሉ እንዳለው ከአትላንቲክ ውቅያኖስ 11 ኪሎ ሜትር ቦታ እና በሁለት የባሕር ኃይለ መርከቦች ላይ የወደቀ ሲሆን አንደኛው መርከብም ለመነሳት ከባድ ክሬን አስፈልጎታል።
የባሕር ኃይሎች፤የባሕር ዳርቻ ጥበቃ መርከቦች እንዲሁም ጠላቂዎች አሁንም የፊኛውን ቀሪ ስብርባሪ እየፈለጉ ነው። ምንም እንኳን ባለሙያዎች የፊኛው ስብርባሪ ባለሥልጣናት ፊኛው ምን ማድረግ እንደሚችል እና መረጃ እንዴት እንደሚያስተላልፍ በተሻለ ሁኔታ ለማወቅ እንደሚረዳቸው ቢናገሩም፣ አሜሪካ ከስብርባሪው ምን የደኅነንት መረጃ እንዳገኘች እስካሁን ግልጽ አይደለም።
የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ጀኔነራል ፓት ራይደር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሜሪካ ተመሳሳይ ፊኛዎች በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ ፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያ ፣ በምሥራቅ እስያ እና አውሮፓ ላይ ሥራ ላይ ውለዋል ብላ እንደምታምን ተናግረዋል። ቃል አቀባዩ አክለውም ፊኛዎቹ ሁሉም ለስለላ ተልዕኮ ጥቅም ላይ የዋሉ ቢሆንም በመጠናቸው እና በችሎታቸው ግን ልዩነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
መረጃውን ከሲኤን ኤን ቢቢሲ እና አልጀዚራ ተጠቅመናል፡፡
በሃና ተሰማ እና ባምላክፈቃድ ፀጋዬ
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት









