

አዲስ አበባ |የካቲት 01 2015 | NBC ETHIOPIA-ጠቅላይ ሚኒስቲር ዐቢይ አሕመድ እና ልዑካቸው በፈረንሳይ ከፕሬዝዳንት ማክሮን ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ መሪዎች በተጠናከረ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና የፈረንሳይ የግሉ ዘርፍ ኢትዮጵያ ቅድሚያ በምትሰጣቸው ዘርፎች ላይ መሳተፍ እንዲችሉ መወያየታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት ማህበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የልዑካን ቡድናቸው ከሰሞኑ በጣሊያንና ማልታ ስኬታማ የሁለትዮሽ ግንኙነትቶችን ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
በፈረንሳይና ኢትዮዽያ መካከል ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዩዽያ ኢንቨስትመንትን እንደሚያበረታቱ ገልፀዋል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው፣ “ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን በማግኘቴ ደስ ብሎኛል። በፓሪስ ስለተደረገልን አቀባበል እናመሰግናለን።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት እየጠነከረ ሲሄድ፣ ወደ ላቀ ኢኮኖሚያዊ ውጤት እንደሚሸጋገር እምነቴ ነው። የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት ለማበረታታት እወዳለሁ።” ብለዋል።
የኢትዩዽያ እና የፈረንሳይ ግንኙነት የሚጀምረው እ.ኤ.አ 1902 ዳግማዊ አፄ ሚኒልክ የእንግሊዙን ንጉስ ኤድዋርድ የንግስና ሥነ-ስርዓት ላይ ለመታደም ሲጓዙ ፈረንሳይ ባረፉበት ወቅት በተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ነበረ፡፡ ያኔ የጀመረውእና አመታትን ያስቆጠረው የሁለትዩሽ ግንኙነት ባለፉት አምስት ዓመታት ይበልጥ መጠናከር ችሏል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በፈረንሳይ አምስተኛው ትልቁ የኤክስፖርት ገበያ እና ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ሁለተኛዋ ትልቁ የንግድ ልውውጥ ማዕከል ነች።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኤ350 አውሮፕላኖችን የሚገዛበት የኤርባስ ኩባንያ ደንበኛ ሲሆን የሀገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር ከፈረንጆቹ ሰኔ ወር 2019 ከማርሴ-አዲስ አበባ አዲስ የአየር በረራ መጀመሩ ይታወሳል።
የፈረንሣይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እ.ኤ.አ. 2019 የኢትዮጵያ በጎበኙበት ለተለያዩ ኢኮኖሚዊ ተግባራት የሚውል የ100 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል
በተጨማሪም የመከላከያ ትብብር ስምምነት የተፈራርሙት ሁለቱ ሃገራት የባህር ሃይልን መልሶ ለመገንባት ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸው የሚታወስ ነው፡፡