፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ነሐሴ 20 2016| NBC ETHIOPIA- የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የ2016 ዓ.ም የፓርቲና የመንግሥት ሥራዎች አፈጻጸም ግምገማ እያካሄደ ነው። የግምገማ መድረኩ በዋናነት የልማትና የመልካም አስተዳደር አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አሥተዳደር እቅድ ትውውቅ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የብሔረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይሉ ግርማይ “የዋግ ኽምራን የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት በጋራ መሥራት እና የቀጣይ የጋራ የልማት እቅድ ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

በውይይቱ በዓመቱ ያጋጠሟቸውን ችግሮች በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ አመራሩ ቁርጠኛ እንዲኾን ያሳሰቡት አቶ ኃይሉ በአካባቢያቸው ያለውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠል በብሔረሰብ አሥተዳደሩ አመራሮች የተሠራው ሥራ አበረታች እንደኾነ ጠቁመዋል።
በግምገማ መድረኩ ላይም የፓርቲው አፈጻጸም እና እቅድ እንዲኹም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ አፈጻጸምና የቀጣይ እቅዶች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በመድረኩ ላይ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የየወረዳው አመራሮችና የሥራ አስፈጻሚዎች በግምገማ መድረኩ ተሳታፊ ሲሆኑ ከነሐሴ 20 እስከ 24/2016 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል መሆኑን የአሚኮ ዘገባ ያመለክታል።












