፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ነሐሴ 20 2016| NBC ETHIOPIA- ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባኤው “የላቀ ትጋት ለትምህርት ጥራትና ለሀገር ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከተሰሩ ጠንካራ ስራዎችየተማሪዎች ምገባ እና ከመጽሀፍት ተደራሽነት ለሌሎች የሀገሪቱ ከተሞቸ ተሞክሮ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል። የመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ ጥራትን የጠበቀና ተደራሽነትን ለማሳደግ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የትምህርትጥራትን ለማረጋገጥ በከተማው የተጀመረው የቅድመ ልጅነት ፕሮግራም ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ከሚሰራቸው ስራዎች የትምህርት ጉዳይ ቀዳሚ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በ2016ዓ.ም በ6ተኛና 8ተኛ ከተማ አቀፍ ፈተና ላይ የተገኘው ከፍተኛ ውጤት በትምህርት ዘርፍ ተሰፋ ሰጪ ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ 31ኛው ከተማ አቀፍ ጉባኤ በ2016 የትምህርት ዘመን የተሻሉ ስራዎች የተሰሩበት መሆን ያነሱ ሲሆን በ6ተኛ እና 8ተኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና 50 እና ከዚያ በላይ ያመጡ ተማሪዎች ከባለፈው ዓመት አኳያ የተሻለ ነው ብለዋል። ሆኖም ግን በውስን ተማሪዎችና መምህራን የሚታዩ የስነምግባር ችግር እንዲሁም አዲሱ ስርዓተ ትምህርትን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ በጥቂት የግል ትምህርት ክፍተት መታየቱን ጠቁመዋል::
በጉባኤው የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ የፌደራልና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በመርሃግብሩ የ2016 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸም ሪፓርት የሚቀርብበት እና የ2017 እቅድ ውይይት የሚደረግበት ነዉ።መድረኩ በነገው ዕለት ነው የሚጠናቀቀው።
በ-ሰላም ይልማ












