
አዲስ አበባ |የካቲት 14 2015 | NBC ETHIOPIA- ቅዳሜ ዕለት በአውስትራሊያ በተደረገው 44ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በሴቶች ወርቅ እንደምታስገኝ ስትጠበቅ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ ኮከብ አትሌት ለተሰንበት ግደይ በውድድሩ የመጨረሻ ላይ ያልተጠበቀ ጉዳት ገጥሟት አሸነፊነትን አጥታላች።
ለተሰንበት የውድድሩን የአሸናፊነት መስመር ልታልፍ ጥቂት ሜትሮች ሲቃርት በድንገት በገጠማት ጉዳት እግሯን ለማዘዝ ተስኗት የድል ሪቫኑን ቀድማ መበጠስ ተስኗት ነበር።
በዚህ ጊዜ የአሸናፊነቱን ክብር ልትቀዳጅ ጥቂት ሲቀራት የወደቀችውን ለተሰንበትን አሰልጣኟ ኃይለ ኢያሱ ወደ ውድድር ሜዳው በመግባት እንድትነሳ በመርዳት የውድድሩን ፍጻሜ መስመር እንድታልፍ ቢያደርጋትም አትሌቷ ከውድድር ውጪ ሆናለች። በዚህም ምክንያት ኬንያዊቷ ቢያትሪስ ቺቤት ውድድሩን ለማሸነፍ በቅታለች።
ለተሰንበት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰች ሲሆን፣ በዚህ አትሌቷን በገጠማት ጉዳይ ዙርያ አሰልጣኝ ኃይለ ኢያሱ ለቢቢሲ እንደተናገረው፣ በውድድሩ ስፍራ በነበረው ከባድ ሙቀት እና ሌሎችም ጉዳዮች ተደራርበው ጫና እንደፈጠሩባት ገልጿል።
የአውስትራሊያው ውድድር ከለተሰንበት አቋም አንጻር ብዙም የማያስቸግራት እና ውጤታማ ልትሆን የምትችልበት የአገር አቋራጭ ውድድር እንደሚሆን አሰልጣኟ ተስፋ አድርጎ ነበር።
በቅዳሜው የአገር አቋራጭ ውድድር ስፍራ የነበረው ሙቀት 30 እና 40 ሴንቲ ግሬድ በመሆኑ ወበቁ ለአትሌቶቹ ፈታኝ ሊሆን ስለሚችል አሰልጣኟ እና ለተሰንበት ሙቀቱን ለመቋቋም የተለያዩ ዘዴዎችን ለመጠቀም ወስነው ነበር ሩጫው የተጀመረው።

አሰልጣኝ ኃይለ እንዳለው ለተሰንበት ውድድሩን በብቃት ለማሸነፍ በሚያስችላት ደረጃ ላይ ነበረች። “በአቅም ደረጃ ለተሰንበት ችግር አልነበረባትም። ለውድድሩ የሚመጥን ብቃት ላይ ሆና ነው የሄደችው።”
ነገር ግን በውድድሩ ስፍራ የነበረው የሙቀቱ መጠን፣ ቀደም ሲል ያደረገቻቸው ተደራራቢ ውድድሮች የፈጠሩባት እረፍት ማጣት እንዲሁም ወደ አውስትራሊያ ያደረገችው ረዥም ጉዞ ባላት ብቃት ላይ ፈታኝ ሁኔታን እንደፈጠረባት ይጠቅሳል።
በውድድሩ ላይ “አንድ ኪሎ ሜትር ሲቀር አወጣጧ ጥሩ አልነበረም። እንዲሁም ሙቀቱ ጋር ተደርቦ ትንሽ የቴክኒክ ችግር ነበር። ፈጥና ነው ዳገቱን የወጣችው። አንዲት ልጅ ነበር የምትፎካከራት ዳገታማ ቦታ ቆርጣ አንድ ሰከንድ ጥላት ሄዳ ነበር” ይላል የመጨረሻውን የውድድሩን ሁኔታ ሲያስረዳ።
ይህ ሁኔታ እና ለተሰንበት እና አሰልጣኟ ከውድድሩ ቀደም ብለው ባወጡት ታክቲክ መሠረት ወደ ፍጻሜው ስትቃረብ ከቀሪዎቹ ተፎካካሪዎቿ ተለይታ ፈጥና ለመውጣት ከተስማሙበት ርቀት እና ጊዜ መሳሳት እንደነበር አሰልጣኙ ለቢቢሲ ገልጿል።
“ይህ የአወጣጥ መዛባት እና ባለው ከባድ ሙቀት ምክንያት በሰውነቷ ውስጥ ያለው ፈሳሽ በላብ አማካይነት በመሟጠጡ (ዲሃይድሬሽን) ከባድ ጫናን አሳድሮባት ወደ መጨረሻው በተቃረበችበት ጊዜ እግሯ ልፍስፍስ ብሎ መራመድ አቅቷት ወደቀች” በማለት የገጠማቸውን አሳዛኝ ሁኔታ ተናግሯል።
ለተሰንበት ግደይ በአሁኑ ወቅት በዓለም ተጠቃሽ ከሆኑ የረጅም ርቀት ሴት ኮከብ አትሌቶች መካከል አንዷ ናት። በዚህም ምክንያት በተለያዩ አገራት በሚካሄዱ ታላላቅ ውድድሮች ላይ በመጋበዝ እንድትሳተፍ በሁሉም የውድድር አዘጋጆች ትፈለጋለች።
አሰልጣኟ ጨምሮም ለተሰንበት የአገር አቋራጭ ውድድሩን ስታደርግ ከረዥም ጊዜ በኋላ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ገልጾ፣ የነበረው ሙቀት ጭቃ፣ አቀበት እና ቁልቁለቱ ሁኔታውን ከባድ እንዳደረገው ጠቅሷል።
ለተሰንበት ግደይ በአውሮፓውያኑ 2017 ነበር ለመጨረሻ ጊዜ የአገር አቋራጭ ውድድር ላይ የተሳተፈችው። ከዚያ ወዲህ ግን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና ጦርነቱን ተከትሎ ለአምስት ዓመታት ያህል የትራክ እንጂ የአገር አቋራጭ ውድድርም ሆነ ልምምድ እንዳላደረገች አሰልጣኟ አስታውሷል።
ለተሰንበት ግደይ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሸናፊ እና ባለ ክብረ ወሰን በመሆኗ በቀጥታ በተጋበዘችበት እና በመጪው ነሐሴ ላይ በሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ውድድር ላይ እንደምትሳተፍ አሰልጣኟ ገልጿል።
ለተሰንበት ግደይ በ10 ሺህ ሜትር፣ በ5 ሺህ ሜትር እና በግማሽ ማራቶች ሦስት የዓለም ክብረ ወሰኖችን የያዘችው አትሌት ስትሆን ባለፈው ዓመት በተካሄደው የዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና ላይ በ10 ሺህ ሜትር አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል።
አሜሪካ ዩጂን ኦሪገን ላይ በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ፤ ለተሰንበት ያስገኘችውን ጨምሮ በአራት ወርቅ፣ በሦስት ብር እና በሁለት የነሐስ ሜዳሊያ ከአሜሪካ ቀድማ ከዓለም ሁለተኛ ሆና ውድድሩን አጠናቃለች።
ሃና ተሰማ
ምንጭ(ቢቢሲ)
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት









