፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 07 2016| NBC ETHIOPIA- 12ተኛው ሀገር ዓቀፍ የፀረ-ተህዋስያን መድሀኒቶች በጀርሞች መለመድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀንን በማስመልከት የጤና ሚኒስቴር ከግብርና ሚኒስቴር ፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ታዳጊ ሀገራት የቲቢ፣ኤች አይ ቪ እና የወባ መድሀኒቶችን ጨምሮ ለሌሎች ህመሞች ፈዋሽ የሆኑ የፀረ-ተህዋስያን መድሀኒቶች በጀርሞች የመላመድ ችግር በስፋት እንደሚስተዋል በመድረኩ ተገልጿል። በዚህም ችግሩ በታዳጊ ሀገራት ላይ አሳሳሲ ደረጃ ላይ ይገኛል ተብሏል።

የፀረ-ተህዋስያን መድሀኒቶች ያለ ጤና ባለሙያ ትዕዛዝ መውሰድ፣ የታዘዙ መድሀኒቶች ማቋረጥ እንዲሁም የታዘዘ መድሀኒት መጠንን በመቀነስ እና በመጨመር መውሰድ ጀርሞች የፀረ-ተህዋስያን መድሀኒትን እንዲላመድ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ቀዳሚዎቹ መሆናቸው ተገልጿል።
በዓለም ከ700ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ያለ አግባቡ የፀረ-ተህዋስያን መድሀኒቶችን በመጠቀማቸው በየዓመቱ ህይወታቸውን ሲያጡ የችግሩ አሳሳቢነት በፍጥነት ካልተገታ እ.ኤ.አ በ2050 ወደ 10ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች እንደሚሞቱ በመድረኩ ተመላክቷል። በተጨማሪም በዓለም የኢኮኖሚ ከ2 እስከ 3በመቶ ኪሳራ የሚያስከትል ሲሆን ይህም በገንዘብ ሲተመን 10 ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደሚያስከትል ተነግሯል።

ፀረ-ተህዋሲያን መድሀኒቶች ከ80 ዓመታት በፊት ተፈልስፈው ለሰው ልጆች ጤና እፎይታን በመስጠት ዓለም ከደረሰባቸው ትላልቅ የሳይንስ ውጤቶች ውስጥ እጅግ ጠቃሚው ነው። በኢትዮጵያ አብዛኞቹ በሽታዎችን ለመከላከል የፀረ-ተህዋስያን መድሀኒቶች ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ።
በ-ሀሴት ኃይሉ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Website – https://nbcethiopia.com/news/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












