፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 15 2016| NBC ETHIOPIA- 211 መንገደኞችና 18 የበረራ ቡድን አባላትን በማሳፈር ከለንደን ወደ ሲንጋፖር በመጓዝ ላይ የነበረው ቦይንግ 777 አውሮፕላን አየር ላይ የመናወጥ አደጋ አስተናግዷል፡፡
አውሮፕላኑ አየር ላይ ባጋጠመው ድንገተኛ የመንገጫገጭ ክስተት በተሳፋሪዎች ብሎም በበረራ ሰራተኞች ላይ ከከባድ እስከ ቀላል ጉዳት አድርሳል፡፡
ከለንደን ከተነሳ ከ11 ስአት በኋላ ሲበር ከነበረበት 37 ሺህ ጫማ ከፍታ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ወደ 31 ሺህ ጫማ መውረዱን ፍላይትራዳር 24 አስታውቋል፡፡
አውሮፕላኑ ከሚበርበት ከፍታ በፍጥነት ዝቅ ማለት የመቀመጫ ቀበቶ ያላሰሩ መንገደኞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ተገልጿል። አውሮፕላኑ አየር ላይ ባጋጠመው መናዋወጥ ሳቢያ በታይላንድ ባንኮክ ሱቫርናብሁሚ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ መገደዱ ተገልጿል፡፡ በተፈጠረው ድንገተኛ ክስተት አንድ የ73 ዓመት እንግሊዛዊ አዛውንት በልብ ድካም ሕይወታቸው ሲያልፍ ከ30 በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ሲ ኤን ኤን ዘግባል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው ተሳፋሪዎች በሕክምና እርዳታ ላይ ይገኛሉ የተባለ ሲሆን አደጋው ከደረሰባቸው ተሳፋሪዎች መካከል መካከል 20ዎቹ በከባድ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡ በርካታ ተሳፋሪዎች የስብራት አደጋዎችን አስተናግደዋል፡፡
በአውሮፕላን ተሳፍሮ የነበረው ዛፍራን አዝሚር የተባለ የማሌዥያ ተማሪ በድንገት አውሮፕላኑ ማዘንበል እና መንቀጥቀጥ ጀመረ፤ ክስተቱን በቃል ለመግለጽ የሚያዳግት እጅግ አስቃቂ ነበር ሲል ተናግሯል፡፡ አውሮፕላኑ በፍጥነት መውረድ ቀበቶ ያላሰሩ መንገደኞችን ከእቃ መጫኛ ጋር ተጋጭተው ወደ ወለሉ እንዲወረወሩ አድርጓል ብሏል ዛፍራን አዝሚር።
ሌላኛው ተሳፋሪ አንድሪው ዴቪስ በረራው የተለመደና ፍጹም ሰላማዊ ነበር ገነር ግን ድንገት አውሮፕላኑ መንቀጥቀጥ ጀመረ በፍጥነትም ወደታች ወረደ ሲል ክስተቱን አስረድታል ፡፡ ክስተቱ ለጥቂት ሰኮንዶች ብቻ ነው የዘለቀው ነገር ግን አውሮፕላኑ የወደቀ ያህል ነበር የተሰማኝ ሲልም ተናግሯል።
አደጋው ከተከሰተ በኋላ አውሮፕላኑ ወደ ባንኮክ እንዲዞር የተደረገ ሲሆን በመጀመሪያው በረራ ላይ ከነበሩት 211 መንገደኞች እና 18 የበረራ ሰራተኞች መካከል 143ቱ በሌላ በረራ ወደ ሲንጋፖር ማቅናታቸውና በሰላም መድረሳቸውን የሲንጋፖር አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጎህ ቹን ፎንግ በፌስቡክ በለቀቁት የቪዲዮ መልእክት ተናግረዋል። ቀሪዎቹ 79 ተሳፋሪዎች እና 6 የአውሮፕላኑ ሰራተኞች አሁንም በባንኮክ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡

አየር መንገዱ በጥቅምት 2000 ከሲንጋፖር ወደ ሎስ አንጀለስ ሲበር የነበረ አውሮፕላኑ በታይዋን ታይፒ ለማረፍ ሲሞክር ተከስክሶ የ83 መንገደኞች ህይወት ከተቀጠፈበት አደጋ ወዲህ ከባድ አደጋ እንዳልገጠመው ሮይተርስ በዘገባው አመላክቷል።
የሲንጋፖር አየር መንገድ በክስተቱ የሰው ሕይወት በማለፉ እና የአካል ጉዳት በመድረሱ እንዲሁም ተሳፋሪዎች አስጨናቂ አጋጣሚ በማሳለፋቸው ይቅርታ ጠይቋል፡፡ አየር መንገዱ በምርመራው ላይ ከባለስልጣናት ጋር በመተባበር እየሰራ ነው የተባለ ሲሆን የሲንጋፖር የትራንስፖርት ሚኒስቴር ክስተቱን እየመረመረ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዓለማችን ግዙፉ የአቪዬሽን ኩባንያ ቦይንግ አውሮፕላን ምርቶች በተደጋጋሚ አደጋዎች እያጋጠማቸው ይገኛል፡፡ ኩባንያው በበርካታ አውሮፕላን ሞዴሎቹ ላይ ከቴክኒክ ችግር በተያያዘ አደጋዎችን እያስተናገደ ሲሆን በምርቶች ላይ የጥራትና የደህንነት ስጋቶች ከፍ ብለው ቀጥለዋል፡፡
የአሜሪካ ፍትህ መስሪያ ቤት ጨምሮ በርካታ የህግ ባለሙያዎች በኩባያው ምርቶች ላይ ተጨማሪ ምርመራዎች እንዲደረጉ ተፅዕኖ ሲያሳድሩ ሰንብተዋል፡፡ የቦይንግ አውሮፕላኖች ላይ ተደጋጋሚ እየደረሱ ባሉ አደጋዎች ተከትሎ በኩባንያው አክስዮን ስያጭ ላይ ተፅእኖ ማሳደሩ ይታወሳል፡፡ንብረትነቱ የሲንጋፖር አየር መንገድ በሆነው ቦይንግ 777 ላይ የተከሰተው አደጋ በቀጣይ በኩባንያው ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ ከወዲሁ ተጠባቂ ሆኗል፡፡












